ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አሁንም ሰላምን ትመርጣለች - አምባሳደር ስለሺ በቀለ

ነሐሴ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሰለፍ ጦርነቱን ቢጀምረውም ኢትዮጵያ አሁንም ለሰላም እጇን ዘርግታለች ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ በውቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሲ ኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው ህወሓት ለሰላም ምንም አይነት ፍላጎት ካለማሳየቱም በላይ ጦርነቱን ጀምሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ግጭቱ የገባችው አሸባሪው ህወሃት የሰው ማእበል በማሰለፍ በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ጉዳት ማድረስ በመጀመሩ ነው ብለዋል።

ካለፈው መጋቢት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊነትን በማስቀደም ተናጥላዊ የተኩስ አቁም ማወጁን ያስታወሱት አምባሳደሩ አዋጁን ተከትሎም ኢትዮጵያ ከሽብር ቡድኑ ጋር ለሚደረገው የሰላም አማራጭ ተሳታፊዎች ማዘጋጀቷን አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተረጅዎች እንዲደርስ በሚልም በኢትዮጵያ በኩል በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ እንደነበር ገልጸው መንግስት የምግብና የመድሃኒት እንዲሁም የእርዳታ ስርጭቱን ለማፋጠን የሚያግዙ የነዳጅና የስልክ አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉን ተናግረዋል።

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በአፋርና በአማራ ክልል ስለወደሙ መሰረተ ልማቶች ከበቂ በላይ ማስረጃዎች እያላቸው ዝምታን ስለመምረጣቸው ያሰመሩበት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ተሳትፎ የተመረጠ በመሆኑ በሁሉም የሃገሪቱ ጫፍ ላሉ ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል ብለዋል።

አምባሳደሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰላም አማራጭ እንዲደረግ መንግስት የፈለገው አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን በመመደብ የመሰረተ ልማት ጥገና ቢያደርግም የሽብር ቡድኑ የጥገና ባለሙያዎችን በመግደልና የመሰረተልማቶቹን በማውደም ጥረቱ እንዳይሳካ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

“በትግራይ ክልል ያለው ቡድን ከሚፈጥረው ትንኮሳ በስተቀር በኤርትና የኢትዮጵያ መካከል ምንም ችግር የለም” ያሉት አምባሳደሩ የሽብር ቡድኑ ላለፉት ሁለት ጦርነቶች በኤርትራ ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን በማድረስ ኤርትራን የቀውሱ አካል ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ነበር ብለዋል።

አሜሪካም ሆነች ሌሎች አካላት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣና ጦርነቱ እንዲቆም ከፈለጉ ጦርነቱን ለሶስተኛ ጊዜ አሸባሪው ህወሃት እንደጀመረው በደንብ ስለሚያውቁ ቡድኑን በማውገዝ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ጫና ሊያደርጉበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም