ህወሃት የለኮሰው ጦርነት የአሸባሪነቱ ማሳያ ነው - ግርሃም ፒብልስ - ኢዜአ አማርኛ
ህወሃት የለኮሰው ጦርነት የአሸባሪነቱ ማሳያ ነው - ግርሃም ፒብልስ
ነሐሴ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህወሃት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የለኮሰው ጦርነት የአሸባሪነቱ ግልጽ ማሳያ ነው ሲሉ ጋዜጠኛ ግርሃም ፒብልስ ገለጹ።
ጋዜጠኛው ካውንተር ፓንች ለተባለው ድረ-ገጽ በላኩት ጽሁፍ እንደገለጹት፤ የሽብር ቡድኑ በለኮሰው ጦርነት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ተስተጓጉላል።
የሽብር ቡድኑ ከባድ ጭካኔዎችን አሳይቶ ከማለፉም በላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የስነልቦና ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡
ቡድኑ የቆሰቆሰው ጦርነት ሰላም እንደማይፈልግ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በመንግስት የተላለፈውን የሰብአዊ ተኩስ ማቆም ውሳኔን ለጦርነት ዝግጅት ማዋሉን አብራርተዋል።
ያለጦርነት መኖር የማይችለው ቡድኑ በመንግስት የተዘረጋን የሰላም አማራጭ ዕድል ላለመጠቀም ተጨባጭነት የሌላቸው ምክንያቶችና ቅድመ ሁኔታዎች መደርደርን ምርጫው ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ላቀጣጠለው ጦርነት ህጻናትና ታዳጊዎችን በገፍ ከማሰለፉም በላይ የአለም የምግብ ፕሮግራም 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ የያዙ 12 ታንከሮችን በመዝረፍ ለዕርዳታ ፈላጊው የክልሉ ህዝብ ያለውን ደንታ ቢስነት ይፋ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ያሉትን ችግሮች በሁሉን አቀፍና አካታች ውይይት ለመፍታት የተቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ የሽብር ቡድኑንም ለማስተናገድ ፍላጎት ቢኖረውም የሰላም ሃሳቡን እንደማይቀበል በመግለጹ የሰላም በሩ እንዲዘጋ እያደረገ መሆኑን ጋዜጠኛው አመላክተዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰላም አማራጭን ለመከተል ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሶስት አስርት አመታት ሲያደርስባቸው በነበረው ግፍና በደል ምክንያት ቡድኑን አምርረው እንደጠሉት ያስታወሱት ጋዜጠኛው፤ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ፣ መንግስት መር ሽብርና የምርጫ ማጭበርበር ምዕራባውያኑ ጠንቅቀው የሚያውቋቸው የድርጅቱ መገለጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል።