የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም መገንባት ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም መገንባት ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን ገለጸ
ነሐሴ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በ2015 በጀት ዓመት አሰራርን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም መገንባት ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።
ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን የ2014 በጀት ዓመት ድርቅ፣ ጦርነት፣ ጎርፍና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱበት ዓመት እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህም የቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የሰብአዊ እርዳታና ሌሎች ምላሾችን በመስጠት የተጠናከረ ሥራ የተሰራበት እንደነበር አብራርተዋል።
በተያዘው 2015 በጀት ዓመት አሰራርን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን የኮሚሽኑ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሰው ኃይልና በፖሊሲ የተጀመሩ የለውጥ ተግባራትን በማጠናከር ለቅድመ ማስጠንቀቂያና አደጋ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጠናከረ ምላሽ መሰጠቱን የክልል ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ እታገኘሁ አደመ በ2014 በጀት ዓመት በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ ገረመው ሊቃ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል የተቻለበት ዓመት እንደነበር ተናግረዋል።