የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የአለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ መዘረፍን በዝምታ ማለፋቸው ለአሸባሪው ህወሃት ቡድን ያላቸውን ግልጽ ድጋፍ ያሳያል - አን ጋሪሰን

701

ነሐሴ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የአለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ በአሸባሪው ህወሃት መዘረፉን እያወቁ ዝምታን መምረጣቸው ለሽብር ቡድኑ ያላቸውን ድጋፍ በግልፅ ያሳያል ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሯ አን ጋሪሰን ገለጹ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ሃላፊ ዴቪድ ቤስሊ የአሻባሪውን ህወሃት ዘረፋ አሳፋሪና አስደንጋጭ በማለት በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸውን ምሁሯ አስታውሰዋል፡፡

ምሁሯ ለግሬይ ዞን ድረ-ገጽ በላኩት ጽሁፍ እንዳመለከቱት፤ አሸባሪው ቡድን የሰላም አማራጭን ትቶ ዳግም ጦርነት መክፈቱን ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ የፈጸመው የነዳጅ ዘረፋ በበርካቶች ዘንድ ውግዘት የገጠመው የነውር ድርጊት መሆኑን አመልክተዋል።

“የትግራይ ህዝብ በከበባ ውስጥ ሆኖ እርዳታ እየቀረበለት አይደለም” በማለት ጩኸት ሲያሰሙ የነበሩት ዋና ዳይሬክተሩ በነዳጅ ዘረፋው ላይ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ ማለፍን መርጠዋል ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ዝርፊያ በትግራይ ክልል የምግብ፤ የማዳበሪያና ሌሎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፎች እንዳይደርሱ የሚያስተጓጉል አሳፋሪ ድርጊት እንደሆነ እየታወቀ ዓለምን በእኩልነትና በገለልተኝነት ይመራሉ የተባሉት ቴድሮስ አድሃኖም ስለዘረፋው እንደማያውቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ህወሃት ከማዕከላዊ ስልጣን በህዝብ ትግል ከተወገደና በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ “በትግራይ ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል” በማለት ቅስቀሳ ማድረግን እንደ ዋና ተልዕኮ በመያዝ ቀጥለውበታል ብለዋል።

ምሁሯ በአፋርና በአማራ ክልሎች ባደረጓቸው ጉብኝቶች የቡድኑ ወረራ የጎዳቸው ተፈናቃዮች በንጽህና፣ በህክምና፣ በምግብና በውሃ እጥረት ሲንገላቱ መመልከታቸውን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም