ቀጥታ፡

አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል- የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ

አዳማ ነሐሴ 27 ቀን 2014(ኢዜአ) አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በኦሮሚያ ክልል በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

May be an image of 3 people, people sitting and people standing

በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታደሰ በዚህ ወቅት እንደገለጹት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በክህሎት ላይ ያተኮረ ከመሆኑም ባለፈ ተማሪ ተኮር የመማር ማስተማር ሂደትን የተከተለ ነው።

ግብረ ገብነትን ትውልዱ ከመሰረቱ ጀምሮ እንዲማርና እንዲያውቅ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸው ከመጪው መስከረም 9/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

"ነባሩ ስርዓተ ትምህርት በይዘት የታጨቀ፣ መምህር ተኮር የሆነና የተማሪዎች ተሳትፎ ማነስ ያለበት፣ ለሀገር በቀል ዕውቀት የሰጠው ትኩረት ያነስ፣ የዘመኑን ክህሎትና ተግባቦት ያላካተተና ልዩ ተሰጦ ያላቸው ተማሪዎችን ከግምት ውስጥ ያለስገባ ነው ሲሉ" አውስተዋል።

አዲሱ ስርዓት ትምህርት ትውልድን በዕውቀት፣ሙያና ክህሎት ለማነፅ ትኩረት ያደረገ ከመሆኑም ባለፈ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተማሪ ተኮር እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ነው ያብራሩት።

በተጨማሪም በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የአይሲቲ፣የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ከ7 እስከ 8 እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ይሰጣል ብለዋል ።

በቢሮው የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ነጋሳ በበኩላቸው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል።

May be an image of 3 people and suit

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ75 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሲተገበር መቆየቱንም አንስተው በተለይ ከክልል ጀምሮ በዞንና በወረዳ ያሉ የስርዓተ ትምህርት ሙያተኞች በቂ ግንዛቤ አግኝተው መምህራን እንዲያዘጉጁ መደረጉን ተናግረዋል ።

የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የመማሪያ መጽሐፎችና የመምህራን መምሪያ ሙጁሎች ተዘጋጅተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍቶች ህትመት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የመምህራን መምሪያ ሙጁሎችና መጽሐፍቶችን በሶፍት ኮፒ ወደ የትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ስራ እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም