ቀጥታ፡

የአውሮፓ ሕብረት አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት ያለ ምንም አሻሚ ሁኔታ በግልጽ ሊያወግዘው ይገባል-መንግሥት

ነሐሴ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት የአውሮፓ ሕብረት ያለ ምንም አሻሚ ሁኔታ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት በግልጽ እንዲያወግዝ ጠየቀ።
መንግስት በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት የማያወላውል ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጿል።
በቤልጂየም፣ሉክሰምበርግና በአውሮፓ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ከአውሮፓ ሕብረት ሃላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ተወያይተዋል።
አምባሳደሯ የተወያዩት በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂንሃ፣ የአውሮፓ የዜጎችና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቢሮ የሰሐራ በታች፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካና ፓሲፊክ ዳይሬክተር አንድሪያ ኩላይማ እና የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ተጠባባቂ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሃንስ ስታውስቡል ጋር ነው።
አምባሳደር ሂሩት ለዳይሬክተሮቹ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በሰጡት ማብራርያ የአውሮፓ ሕብረት አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ዳግም ጦርነት በማያሻማ መልኩ በግልጽ እንዲያውግዘው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት የማያወላውል ቁርጠኝነት አለው ብለዋል።
የተደረገው ግልጽና ገንቢ ውይይት የአውሮፓ ሕብረት አመራሮች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የተሻለ አረዳድ እንዲኖራቸው ያደረገ ነው ሲል በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።
የመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ባወጣው መግለጫ የሕወሓት የሽብር ቡድን እየደረሱ የሚገኙ ጥፋቶችን ለማስቆም መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ያደረጋቸው ጥረቶች ሁሉ እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ፣ አሸባሪውን ሕወሐት መጫን ሲገባቸው "ሁለቱም ወገኖች" በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው ተቀባይነት የለውም ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም