በ'በጎ ሰው ሽልማት' በተሰማሩበት ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ለበርካቶች አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በ'በጎ ሰው ሽልማት' በተሰማሩበት ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ለበርካቶች አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ተችሏል

ነሐሴ 27 ቀን 2014(ኢዜአ) በ'በጎ ሰው ሽልማት' በተሰማሩበት ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ለበርካቶች አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለሕዝብ ማስተዋወቅና አገር እንዲያከብራቸው ማድረግ ተችሏል ሲል የበጎ ሰው ሽልማት ቦርድ ገለጸ።
የበጎ ሰው ሽልማት ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ኢትዮጵያዊያንን በየዓመቱ ዕውቅና የሚሰጥ ሽልማት ነው።
"በጎ ሰዎችን በመሸለምና እውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መሪ ሀሳብ በየዓመቱ የሚከናወነው ይኼ የሽልማት ዝግጅት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሲከናወን ቆይቷል።
ዘንድሮም ለአሥረኛ ጊዜ በ11 ዘርፎች እንደሚከናወን ቢጠበቅም በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ በቂ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ባለመጠቆማቸው ልዩ ተሸላሚ የሚለውን ዘርፍ ጨምሮ በአሥር ዘርፎች ብቻ ይከናወናል።
የበጎ ሰው ሽልማት የቦርድ አባል አቶ ነፃነት ተስፋዬ የበጎ ሰው ሽልማት በአርአያነታቸው በርካቶች ማስተማር የቻሉ ግለሰቦች እውቅና ተስጠቷል ይላሉ።
ሽልማቱ እውቅና የተቸራቸው ግለሰቦች ለተሻለ ተግባር እንዲነሳሱ ያደረገና ተተኪው ትውልድም ተስፋ እንዲሰንቅ ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተሰማሩበት ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ለበርካቶች አርዓያ የሆኑ ግለሰቦችን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ማስቸሉን ነው የጠቆሙት።
በሌላ በኩል በበጎ ሰው ሽልማት ከተካተቱት መወዳደሪያዎች አንዱ የሆነውን የማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ በየዓመቱ ዕጩዎች በሚፈለገው ልክ እየተጠቆሙ አይደለም ብለዋል።
በየዓመቱ በቂ የተወዳዳሪ ዕጩዎች ስለማይጠቆሙና የሚጠቆሙትም በዘርፉ የሚካተቱ ባለመሆናቸው በሁሉም ዓመት መሸለም እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት።
በመሆኑም በእያንዳንዱ የጥቆማ መቀበያ ጊዜም ለማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ ትኩረት እንዲደረግ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ጥሪ ማድረግ ቀጥለናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት፣ የጥናትና ምርምር ማዕከሎችና በተለያየ መስኮች ተሰማርተው የሚሰሩ ሰዎች ጭምር ጥቆማ እንዲያቀርቡ እያሳሰቡ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
የገንዘብ ሽልማትን በተመለከተ ከተመልካች የሚነሳውንም ሀሳብ እየተከታተሉት እንደሆነ ገልፀው ከሲቪክ ማኅበራት ቦርዱ ዕውቀና ስላገኘ የገንዘብ ሽልማት መስጠት እንደሚችል ገልፀዋል።
በቀዳማዊ ኃለሥላሴ ዘመን የነበረውንም የሽልማት ተሞክሮ ለአብነት ያነሱት አቶ ነፃነት ለተሸላሚዎች ከዕውቅና ባሻገር የገንዘብ ተሸላሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የበጎ ሰው ሽልማት ዘርፍ በመምህርነት፣ በሳይንስ፣ በኪነጥበብ፣ በበጎ አድራጎት፣ በቢዝነስና ሥራ ፈጠራ፣ በመንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስና ባህል፣ በማኅበራዊ ጥናት፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ሽልማት ይሰጣል።
በተጨማሪም ለሀገሪቱ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያዊያንንም በልዩ ተሸላሚነት የሚሸልም ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው።
10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት የፊታችን ነሐሴ 29 ቀን በአዲስ አበባ እንደሚከናወን የበጎ ሰው ሽልማት ቦርድ መረጃ ያመለክታል።