የቆዳና ቆዳ ውጤቶች መሸጫ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ ውስጥ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የቆዳና ቆዳ ውጤቶች መሸጫ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ ውስጥ ተከፈተ
ነሐሴ 27 ቀን 2014(ኢዜአ) የቆዳና ቆዳ ውጤቶች መሸጫ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ ውስጥ በይፋ ተመርቆ ተከፈተ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ማዕከሉን በይፋ የመረቁ ሲሆን ለገበያ የቀረቡ የቆዳ ውጤቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በማዕከሉ ስምንት አቅራቢዎች የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ይዘው ቀርበዋል።
የሴቶች ቦርሳ፣ ዋሌት፣ መጫሚያዎች፣ ጃኬቶችን ጨምሮ በርከት ያሉ የቆዳ ውጤቶች በመሸጥ ላይ ሲሆን ማዕከሉ እውን እንዲሆን ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በጋራ ተንቀሳቅሰዋል።
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን የሚያስተናግድ መሆኑ ለቆዳ ውጤት አቅራቢዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን አብራርተዋል።
"በማዕከሉ ብቻ እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ድረስ የውጭ ምንዛሬ ሊገኝ እንደሚችል ጥናቶች አመላክተዋል" ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ጅምር በማስፋት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ይሰራል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በማዕከሉ ሥራ የጀመሩ አቅራቢዎች ከ200 ሺህ ዶላር በላይ ግብይት መፈጸማቸውንም ጠቅሰዋል።
የቆዳ ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ የድጋፍ መርሃ-ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ያሉት አቶ መላኩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አንዱ አካል መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ታጠቅ ይርጋ በበኩላቸው፤ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ፣ በሥራ እድል ፈጠራና እሴት በመጨመር ላይ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ በመንግሥት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የቆዳ ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ ግብዓት አቅርቦት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የኬሚካል ግብአት፣ እንዲሁም መለዋወጫዎች አቅርቦት ላይ መሰራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቆዳ ውጤቶችን ይዘው ከቀረቡት መካከል 'ኬር ኤይዚ' ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መራዊ በሰጡት አስተያየት እንደዚህ ዓይነት እድል መመቻቸቱ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
ሥራ በጀመርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር እያገኘን ነው ሲሉም ነው የገለጹት።
የ'ዘመንአሞር አዲስ' የቆዳ ውጤቶች አቅራቢ ኩባንያ ባለቤት ዘመንአሞር ተፈራ በበኩላቸው፤ የኮሮና ቫይረስ በእጅጉ ከተፈተነ በኋላ ይህ እድል መምጣቱ ተጎድቶ የነበረውን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታውሰዋል።
"እዚህ ስንገበያይ በዶላር ነው የምንሸጠው ሌሎችም እድሉ እንዲመቻችላቸው በሰፊው ሊሰራበት ይገባል" ብለዋል።
2014 በጀት ዓመት ከቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ 40 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።