አምባሳደር ስለሺ በቀለ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ስለሺ በቀለ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያዩ
ነሐሴ 27 ቀን 2014(ኢዜአ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያዩ።
አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እና የሰሜን ወሎ ሐገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ጋር ነው የተወያዩት።
በውይይቱ ሁለቱ የእምነት አባቶች ምዕመናኑን አስተባብረው ለተጎዱት በመድረስ እና በመደገፍ እንዲሁም የአገር አንድነትን ለማጎልበት ለሚያደርጉት አርዓያነት አምባሳደር ስለሺ ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በገጠማት ፈተና የተፈናቀሉትን በማስጠጋት፣ እርዳታ በማሰባሰብ፣ በማጽናናት ያሳዩትን አለኝታነት ለአብነት ማንሳታቸውን ዋሽንግተን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅትም በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ወገኖች ከአገራቸው ጎን እንዲቆሙ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በያሉበት አካባቢ እንዲያስረዱ እና ለአንድነታችን ዘብ እንዲሆኑ አባታዊ ምክራቸውን እንዲቀጥሉ አምባሳደር ስለሺ ጠይቀዋል።
የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል በውይይቱ እንዳሉት በሶስቱ ግዛቶች የሚኖረውን ዳያስፖራ በማስተባበር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረስ እና የአካባቢው የመንግስት ተመራጮች ሚዛናዊ እይታ እንዲኖራቸው የሚደረገው ስራ እንደሚጠናከር ቃል ገብተዋል።
የሰሜን ወሎ ሐገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስም በበኩላቸው በተለይም ወልድያና አካባቢው በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን በመጥቀስ፤ ቤተክርስትያን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በሐይማኖት እና በሌላ አመለካካት ሳትለይ መጠጊያ ሆና ቆይታለች ብለዋል።
አካባቢው አሁንም ከስጋት ቀጠና የወጣ ባለመሆኑ እና የተጎዱ የእምነትና የአገልግሎት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።