የህወሓት የሽብር በድን የፈፀመውን ወረራ ለመመከት ከፀጥታ ሀይሉ ጎን እንቆማለን---የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት የሽብር በድን የፈፀመውን ወረራ ለመመከት ከፀጥታ ሀይሉ ጎን እንቆማለን---የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች

መተማ (ኢዜአ) ነሐሴ 26/2014 ሀገር የማፍረስ ግብ ይዞ ጦርነት የከፈተውን ህወሓት ለመመከት ለፀጥታ አካላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት በላይ አስማማው እንደተናገረው፣ አሸባሪው ህወሓት የፈፀመውን ወረራ ለመመከት ሁሉም የበኩሉን ማገዝ ይኖርበታል።
ሃገርን ከነክብሯ ለማቆየት በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ስንቅና አስፈላጊውን ድጋፍ በማቅረብ አጋርነትን ማሳየት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነም ገልጿል።
ዛሬ ደም በመለገስ ከፀጥታ አካላት ጎን መቆሙን በተግባር ማሳየቱን ጠቅሶ፤ በቀጣይም የሚጠበቅበትን ለመደገፍ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
"ከዚህ በፊት በከተማችን ሰርጎ ገቦች እንዳይገቡ ተገቢውን ጥበቃ ከማድረግ ባሻገር ወደ ግንባር በመሄድ ጠላትን ተፋልመናል" ያለው ወጣቱ፣ አሁንም የሽብር ቡድኑ የጀመረውን ወረራ በብቃት ለመመከት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።
ሌላኛው ወጣት ቴዎድሮስ ደሳለኝ በበኩሉ፣ "ኢትዮጵያ በየትኛውም ኃይል የምትፈርስ ባትሆንም የስቃይዋ ጊዜ እንዲራዘምም መፍቀድ አይገባም፤ ከስቃዩዋ መታደግ አለብን" ብሏል።
የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችን ከመደገፍ ባለፈ መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ መሆኑን ነው ወጣቱ የገለጸው።
"አሸባሪው ህወሓት በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደጎን ትቶ ወደ ጦርነት መግባቱ የቡድኑን ግብዓተ መሬት የሚያፋጥን ነው'' ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ወጣት ሀሊማ አደም ነች።
ከዚህ በፊት ህወሓት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በእጁ አድርጎ ሽንፈትን የደረሰበት በህዝቡ አንድነትና ትግል መሆኑን አስታውሳ፣ አሁንም ሀገርን ለማዳን ሴት ወንድ ሳይባል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣና እሷም ለእዚህ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
አካባቢዋን ከሰርጎ ገቦችና ሀሰተኛ ወሬ ነጋሪዎች በመጠበቅና በስንቅ ዝግጅት የበኩሏን እገዛ እንደምታደርግም ነው ወጣቷ የገለጸችው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው፣ "አሸባሪው ህወሓት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ያልተቀበለው ካለጦርነት መኖር እንደማይችል በማረጋገጡ ነው" ብለዋል።
ህዝቡ በጠላት ወሬ ሳይወናበድ እንደተለመደው ጠላት በመረጠው መንገድ አስተናግዶ ድል ማድረግ እንደሚችል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት ስንቅና ትጥቅ ከማቅረብ ባለፈ በግንባር ጠላትን ለመፋለም ዝግጁነቱን አረጋግጧል።
ቀደም ሲል ወደ ሱዳን ሾልኮ የወጣው የህወሓት ቡድን በተደራጀ አግባብ በአካባቢው ጥቃት ለመፈጸም ሞክሮ ማክሸፍ እንደተቻለ አቶ ቢክስ አስታውሰዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ሆኖ ጠላትን ድል ለመምታት ዝግጁነቱን ማረጋገጡን ተናግረዋል።
ለሚመጣው ግዳጅ ሁሉ ህዝቡ ''በአንድ እጁ ማረሻ በሌላኛው እጁ ደግሞ መሳሪያውን'' ይዞ በተጠንቀቅ የቆመ መሆኑን አመልክተዋል።