የጠላትን ሃይል ለመመከት በጋራ እንሰራለን- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የጠላትን ሃይል ለመመከት በጋራ እንሰራለን- ምክር ቤቱ
ሐዋሳ፤ ነሐሴ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)፡ ጦርነት ያወጀውን አሸባሪው ህወሓት በአንድነት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን የሲዳማ ክልል ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ የኋላሸት በቀለ እንዳሉት የጋራ ምክር ቤቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው መክሯል።
በውይይቱ እንደ ሀገር የተጀመሩ የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን ፓርቲዎች በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የጀመራቸውን የሰላም አማራጭ አጠናክሮ እንዲቀጥል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መጠየቃቸውን አመላክተዋል።
አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚገባም ምክር ቤቱ የጋራ አቋም መያዙን ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑን በጋራ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ፓርቲዎች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ሰላም የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉና በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውጤታማነት ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል ፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ አሸባሪው ህወሓትን በግንባር እየተፋለመ ላለው ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገውን ደጀንነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ያወጣውን ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ ምክትል ሰብሳቢው አቶ በለጠ ሲጌቦ አቅርበዋል፡፡
በአቋም መግለጫው የትግራይ ህዝብ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ልጆቹን ወደ ጦርነት ከመላክ እንዲቆጠብና የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ከሆነው አሸባሪ ቡድን ራሱን እንዲጠብቅ ተጠይቋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በሚደረገው ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ክልላዊ የፓለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም ግንባሮች ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ለመቆም ቁርጠኛ መሆናቸው ተመላክቷል።
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርንና ህዝብን ለማዳን ከመንግስት ጎን በመቆም በትበብር እንዲሰሩ በአቋም መግለጫቸው ተጠቅሷል።
የጋራ ምክር ቤቱ መላው የክልሉ ህዝብ፣ ሴቶችና ወጣቶች የህወሓትን ዜራ ለማክሸፍ የሚደረገውን ትግል በሁሉም መስክ እንዲደግፉ በአቋም መግለጫው ጠይቋል።
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችለው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል፡፡
በጋራ ምክር ቤቱ ሶስት ክልላዊና ዘጠኝ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ተመላክቷል።