ቀጥታ፡

የትግራይን ህዝብ ለዳግም ጦርነት እየዳረገ ያለው አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊ ውግንና የሌለውና አሸባሪነቱን የሚያሳይ ነው- የመከላከያ ሚኒስትር

ነሐሴ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የትግራይን ህዝብ ወደ ዳግም ጦርነት ያስገባው አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊ ውግንና የሌለውና አሸባሪነቱን የሚያሳይ መሆኑን የመከላኪያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ ተናገሩ።

ከሽብርና ጦርነት ውጭ ሌላ ህልውና የሌለው አሸባሪ ህወሃት ለ3ኛ ጊዜ የትግራይን ህዝብ ወደ ጦርነት ማስገባቱንም ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ በመግለጫቸው የተዘረጋን የሰላም አማራጭ በመናቅ ሌላ ዙር ጦርነት ማወጁ የቡድኑ ተፈጥሯዊ ባህሪ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ከትግራይ ህዝብ ጥያቄ በመፍራትና የሌሎች ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በማለም ዳግም የጀመረው ጦርነት መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተለየ ሀሳብና አጀንዳ መቀበልና መስማት የማይሻ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ የተለዬ ሃሳብ ያለውን አካል እየገደለና እያስወገደ የመጣ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል።

በንግግርና በሰላም አምኖ ችግር የፈታበት አንዳችም የታሪክ አጋጣሚ የለም ሲሉም አረጋግጠዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በቀሰቀሰው ጦርነት የትግራይ ህዝብ ክፉኛ መጎዳቱን አስታውሰው ህዝቡ ሰላም ባለማግኘቱ ጥያቄዎችን የማቅረብ እድል መነፈጉንም ይናገራሉ።

የትግራይ ህዝብ ሰላም ካገኘ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳል በሚል ስጋት የሰላም በሮችን በመዝጋት በጦርነት አማራጭ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በዚህም ቡድኑ "ልጆቻችን የት አሉ" የሚለውን የክልሉን ህዝብ ጨምሮ በባለፈው ጦርነት ህዝቡ የደረሰበትን ጉዳት ስለሚጠይቅና ዕድሜዬ ያጥራል በማለት በስጋት ውስጥ ሆኖ እየፈፀመ ያለው ወንጀል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ የትግራይ ህዝብ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች የቤት ስራን ተቀብሎ እየሰራበት ያለ ነው ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ የጦርነት አውዳሚነት በታሪኩ የተረዳ ሰላም ፈላጊ ህዝብ መሆኑን ገልጸው የጥፋት ቡድኑ ባለው ድብቅ ፍላጎት ሀሰተኛ ፕሮፓጋነዳ እየነዛ ህዝቡን ለሌላ ዕልቂት እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ህወሓት የሀሰት ትርክትና ፕሮፖጋንዳ በመፍጠር የትግራይ ክልል ህዝብ ለዘመናት በሠላምና በአንድነት አብሮ ከኖረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመለያየት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት መንግሥት ረጅም እርቀት ተጉዞ የሠላም ጥረት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።  

አሁንም ቢሆም መንግሥት ለሠላም የዘረጋውን እጅ ሳያጥፍ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በተደጋጋሚ የሰላም አማራጭን ቢያቀርብም አሸባሪው ህወሃት የሰላምን መንገድ በመዝጋት በጥፋት እንቅስቃሴው መቀጠሉን ገልጸዋል።

መንግስት የዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት የትግራይን ህዝብ በማደናገርና በማስገደድ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ያስገባው ተጠያቂነት እንዳይኖር አጀንዳ ለመፍጠር እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ፣ በዲስፕሊኑና በህዝባዊነቱ የሚታወቅ ሰራዊት እንደሆነ ገልጸው፤ ከለውጡ በኋላም ሰራዊቱ በዕውቀት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራና ኢትዮጵያን የሚመስል ሰራዊት ስለመገንባቱ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት አሸባሪውን ህወሓት ጨምሮ ከማንኛውም ወገን የሚሰነዘርን ጥቃት በብቃት መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም