ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

ነሐሴ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ መድን ድርጅት 35ኛ ዓመታዊ የሥራ አመራር ጉባዔውን አካሂዷል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ፤ በጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ድርጅቱ በ2014 በጀት ዓመት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ከአረቦን ገቢ መሰብሰቡን አብስረዋል።

ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ446 ሚሊዮን ወይም የ7 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የካሣ ክፍያ በመፈጸም በታሪኩ ከፍተኛው አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸው፤ የተከፈለው የካሣ ክፍያም በአብዛኛው ከጠለፋ ዋስትና ሰጪ አጋሮች ተመላሽ ተደርጓል ብለዋል።

ድርጅቱ ከኢንቨስትመንት፣ ከወለድ፣ ከሕንፃ ኪራይና ከሌሎች ገቢዎች ከ528 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በ2014 በጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ነው የተናገሩት።

የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ17 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ላስተናገደችው ከ166 ሺህ በላይ ውሎች የሰጠው የዋስትና ሽፋን 4 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ጨምሮ አገራዊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችና በዩክሬንና ራሽያ ጦርነት ሳቢያ ዓለም አቀፍ ዋጋ ንረት ለዘርፉ ዕድገት ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ለአብነትም በአቬዬሽን ኢንዱስትሪው በኮቪድ-19ና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ጋር ተያይዞ  ከተያዘው ዕቅድ የ562 ሚሊዮን ቅናሽ ማሳየቱን አስረድተዋል።

የድርጅቱ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ለማ ጉዲሳ፤ ኢትዮጵያ መድን በሚሰጣቸው አገልግሎቶች አገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎችን ወደ ፊት ለማራመድ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ከተመሰረተ 47 ዓመታት ያስቆጠረው ድርጅቱ የመድን ኢንደስትሪ ገበያውን ድርሻ በመሪነት ይዞ ከትርፍ ባሻገር ለሠራተኞች፣ ሽያጭ ወኪሎችና ሌሎች ዜጎች የሥር ዕድል በመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳላው ገልጸዋል።

ድርጅቱ ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም በመድን ሽፋን ለሚሰጣቸው ደንበኞቹ የተሻለ ካሣ ክፍያ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያስችለዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በበጀት ዓመቱ ብቻ ለተለያዩ አካላት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በመለገስ  ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደተወጣም ተገልጿል።

በጀት ዓመቱ ከአገሪቷ መድን ኢንዱስትሪ 16 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከዐረቦን መጠን የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 15 ነጥብ 3 ቢሊዮኑ ከጠቅላላ መድን፤ 1 ነጥብ 4 ቢለዮን ደግሞ ከሕይወት መድን የተገኘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም