የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ህወሃት የሰላሙን አማራጭ እንዲቀበል በማስገደድ በቃህ እንዲሉት የጋሞ አባቶች ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ህወሃት የሰላሙን አማራጭ እንዲቀበል በማስገደድ በቃህ እንዲሉት የጋሞ አባቶች ጥሪ አቀረቡ
አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ህወሃት በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል በማስገደድ በቃህ እንዲሉት የጋሞ አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጋሞ አባቶች ፤ ቡድኑ ጦርነት አጥፊ መሆኑን እያወቀ የሰላም አማራጭ መጠቀም አለመቻሉ የክፋቱን ጥግ የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ተፈራ ኦይቻ ፤ ኢትዮጵያ የሰው ሃይሏንና የተፈጥሮ ጸጋዎቿን በማስተሳሰር ወደ ዕድገት ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ከአብራኳ በወጡ ልጆቿ በጦርነት መፈተኗ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡
በጥፋት ድርጊቱ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሃት መንግስት በሆደ ሰፊነት ታግሶት የተሰጠውን የሰላም አማራጭ መጠቀም አለመቻሉ የክፋቱን ጥግ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑ ለሰብአዊ ድጋፍ ማስፈጸሚያ ተብሎ የተላከውን ነዳጅ በመስረቅ ለጦርነት ዓላማ ማዋሉ ለትግራይ ህዝብ ምንም ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጦርነት ዜጎችን ለእልቂትና ሀገርን ለኪሳራ ከመዳረግ ባለፈ ጥቅም የሌለው አስከፊ ተግባር በመሆኑ ቡድኑ የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ሊቀበል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ይህ ጦርነት በዋናነት የሚጎዳው የትግራይ ክልል ህዝብ ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌው፤ ህዝቡ ህፃናት ልጆቹን ጭምር በጦርነት እየማገደ ያለውን ቡድኑን በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል በማስገደድ በቃህ እንዲለው ጥሪ አቅርበዋል።
በጋሞ ህዝብ ዘንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ከእልቂት ይልቅ ለእርቅ ሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያወሱት አቶ ተፈራ ፤ የትግራይ አባቶች፣ እናቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራንም እልቂቱን ለማስቆም የበኩላቸውን እንዲወጡ መክረዋል፡፡
ቡድኑ የህዝቡን አንድነትና ጽናት ለመጉዳት ለሚያሰራጨው የሀሰት ወሬ ጆሮ ባለመስጠት የኢትዮጵያን አንድነት ለመጪው ትውልድ ጠብቆ የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ አለብን ብለዋል።
ሌላው የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ አዳሙ ኪሮ በበኩላቸው ፤ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ በመከባበርና በመፈቃቀር ለዘመናት የኖረውን ህዝብ አንድነቱን የሚጎዳው ይህ ጦርነት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ጦርነት ከሰብአዊ ቀውስ ባለፈ የተፈጥሮ ሀብቶችንም ጭምር የሚያጠፋ በመሆኑ ለህዝብና ሀገር ደህንነት ሲል መንግስት በሆደ ሰፊነት የሰጠው የሰላም አማራጭ ዕድል ተገቢነት ያለው ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በትግራይና በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የምንገኝ ህዝቦች ማንም ሊለያየና ሊከፋፈለን የማይችል በአንድ የተጋመድን መሆናችንን በመረዳት ለእልቂት ሆን ብሎ የተነሳውን ህወሓት ለማስቆም የትግራይ አባቶችና እናቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጦርነት በጦርነት ሳይሆን በመነጋገር ነው መቋጫ የሚያገኘው ያሉት አቶ አዳሙ፤ ህወሃት ከጦርነት ይልቅ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዕድል እንዲጠቀም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ህዝቡ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚለቀቁ የተሳሳተ መረጃ ሳይሸበር የአካባቢውን ሰላምና አንድነቱን ማስጠበቅ፣ በተለይ ለሀገር ደህንነት በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡