ቀጥታ፡

የጠላቶች ሴራ ያልበገረው የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ

ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ መልከ-ብዙ ውስጣዊ እንዲሁም ውጫዊ ፈተናዎችን አስተናግዳለች።

በእነዚህ ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ እንደ ማንኛውም የዓለም ክፍል ኢትዮጵያም ተፈትናለች።

ከኮቪድ-19 በተጨማሪ በጎርፍና የድርቅ አደጋም በከፍተኛ ሁኔታ ተፈትናለች።

ከሁሉም በላይ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የሰላምና መረጋጋት ችግር ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ከመሆኑ በላይ የሕዝቡን ኑሮም አዛብቷል።

በአሸባሪው ህወሓት የተጀመረው ጦርነትም በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ችግርና አለመረጋጋት የፈጠረ መሆኑ ይታወቃል።

በጦርነቱ ሸኔ የመሰሉ የውስጥ ባንዳዎችና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አገር ለማፍረስ ያልሞከሩት ሴራ አልነበረም።

ዛሬም ቢሆን ከያሉበት ተጠራርተው ኢትዮጵያን ለማንበርከክና የልማት ጉዞዋን ለመግታት ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው ለጥፋት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ግን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው በጽናት በመቆም ጠላትን ከመመከት ባሻገር አስደናቂ የልማት ሥራዎችን በመከወን ላይ ይገኛሉ።

"ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት" በሚል እሳቤ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የ10 ዓመት የልማት እቅድ እየተገበረች ትገኛለች።

በዚሁ መሰረት ባለፉት አራት ዓመታት በተለይም በግብርና ልማት ትልቅ ውጥን ይዛ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት አስመዝግባለች።

በመኸርም ይሁን በበጋ መስኖ ልማት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ የውስጥ ፍጆታን መሸፈን ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም ለማቅረብ እየሰራች ትገኛለች።

በተለይም በስንዴ ልማት የኦሮሚያ ክልል የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የባሌ እና የአርሲ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በዚህ ዓመት በባሌ ዞን ብቻ 154 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ የለማ ሲሆን ይህም ትልቅ እምርታ መሆኑ ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ''የስንዴ ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ሆኖ የሚቀረው 4 ሺህ፣  5 ሺህ ሄክታር በክላስተር ማልማት ልማድ ሲሆን ነው'' ይላሉ።

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቸራትን እምቅ አቅም ተጠቅማ ከራሷ ዜጎች አልፋ ለሌሎች የምትበቃ አገር መሆኗንም ገልጸዋል።

''ተባብረን ከተጓዝን ከበቂ በላይ ሀብት አለን፤ ኢትዮጵያዊያን ቆም ብለው ልመና በቃን፤ ድህነት በቃን፤ ማለት አለባቸው'' ብለዋል።

ይህ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር መሥራት እንደሚቻል በተግባር ማሳየት እንደተቻለም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል በበጋ መስኖ የለማ ስንዴ ከጎበኙ በኋላ በክልሉ በሁለት ዞኖች ከታረሰ እርሻ መሬት ብቻ ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

ይህ ደግሞ በተለይም ከሶማሌ ክልል መሆኑ ከዚህ በፊት ተጥሎና ተረስቶ ከነበረው ቆላማ አካባቢ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ከተጀመረ ወደ አራት ዓመታት ያስቆጠረው የመስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱንም ይናገራሉ።

በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚመረት የመኸር እርሻ የኢትዮጵያን 75 በመቶ ፍላጎት ብቻ እየሸፈነ ይገኛል።

የመስኖ ስንዴ ማምረት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የአገሪቷን 60 በመቶ መሬት የሚሸፍነውን ቆላማ አካባቢ ላይ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን በደጋው አካባቢ ደግሞ በኦሮሚያ ደጋማ አካባቢዎች መስፋፋቱን ይገልጻሉ።

ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት 3 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ መሞከሩን አስታውሰው፤ ዘንድሮ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መድረሱን አንስተዋል።

በቀጣይም በ1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ በማምረት በአማካይ ወደ 40 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዷል።

ይህ ማለት ደግሞ የአገር ውስጥ የስንዴ ፍጆታን ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ከግብርና ልማት ዘርፉ ባሻገር ኢትዮጵያ በቱሪዝም ልማት ዘርፍም ስኬታማ ሥራዎች እያከናወነች ትገኛለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የእንጦጦ ፓርክን አልምቶ ሥራ ማስጀመር የተቻለ ሲሆን አንድነት ፓርክና የወዳጅነት አደባባይም ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም የጎርጎራ፣ ኮይሻና የወንጂ ኢኮ-ቱሪዝም ልማትና ሌሎች በየአካባቢው የቱሪዝም መስህብ ማልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ኢትዮጵያ የሚያስደንቁ ውብ መስህቦች ያላት አገር በመሆኗ በየዓመቱ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት የሚቻል ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የእንጦጦ ፓርክን በባለሀብቶች ድጋፍና ትብብር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመገንባት ማጠናቀቅ መቻሉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም