ዓለም አቀፍ ፈተናዎችና የአገር ውስጥ ውስብስብ ችግሮች እያሉ የተመዘገበው የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ ተስፋ የታየበት ነው- የዘርፉ ምሁር - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ፈተናዎችና የአገር ውስጥ ውስብስብ ችግሮች እያሉ የተመዘገበው የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ ተስፋ የታየበት ነው- የዘርፉ ምሁር
ነሃሴ 26/2014/ኢዜአ/ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችና የአገር ውስጥ ውስብስብ ችግሮች እያሉም በ2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የተመዘገበው የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ ተስፋ የታየበት መሆኑን አንድ የኢኮኖሚ ምሁር ተናገሩ።
በአውሮፓዊያኑ 2019 በቻይና ውሀን የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከመቅጠፍ ባለፈ በኢኮኖሚ ላይም ቀላል የማይባል ጫና አሳርፏል፡፡
ኢትዮጵያም በዚሁ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በመፈተን በጤና፣ ኢኮኖሚና አጠቃላይ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና አርፎባታል።
ከኮሮና ወረርሽኝ በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች በአንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ሲደረግ የነበረው ያልተገባ ጫናም ሌላ ፈታኝ አጋጣሚ መሆኑ ይነሳል።
በ2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት ሰላም ለማስከበር ሲል ተገዶ የገባበት ጦርነትና ሌሎች የሰላም እክሎችም ተደማሪ ፈተና ሆነዋል።
እነዚህና ሌሎችም በርካታ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችና የውጭ ጫናዎች ተደራርበው የኢትዮጵያ የፈተና ወቅቶች መሆናቸው ይነገራል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ሆናም በተለይም በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እየሱስወርቅ ዛፉ፤ ኢትዮጵያ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆና በ2014 በጀት ዓመት ያስመዘገበችው የምጣኔ ሃብት እድገት አስደናቂ መሆኑን ይናገራሉ።
በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና ከ6 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰው፤ ጫናዎች ባይኖሩ ምን ያህል የላቀ ውጤት ይገኝ እንደነበር አመላካች ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለይም ከወጪ ንግድ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት ለማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም መሻሻል ጉልህ ሚና እንደነበረው መገለጹ ይታወሳል።
የወጪ ንግዱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን የወጪ ምርቶችን በአይነት፣ ብዛትና ጥራት ማሻሻል መቻሉም ሌላው ምክንያት ሆኗል።
በበጀት ዓመቱ ከቡና ምርት ከተገኘው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ባሻገር የማዕድን ምርት የወጪ ንግድም በአማካይ 64 በመቶ ሲያድግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድም በ26 በመቶ ማደግ ችሏል።
በዚህም አጠቃላይ ለኢኮኖሚ እድገቱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ የስኬቱ ቁልፍ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እየሱስወርቅ ዛፉ ያብራራሉ።
በመሆኑም መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት ለግብርናው፣ ለአገልግሎቱና ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል ሌሎች ተግባራትንም በማከል በ2015 የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመንግሥት በኩል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ይታወቃል።