ቀጥታ፡

የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ምክር ቤት ለማቋቋም በረቂቅ የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

ነሃሴ 26/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ምክር ቤት ለማቋቋም በረቂቅ የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ውይይት መደረግ መጀመሩን የምክር ቤቱ አደራጅ አስታወቀ።

በኢትዮጵያያሉየኃይማኖትተቋማትበስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት በመገናኛ ብዙሃንም ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሰሩ ነው።

ለዚህም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማሰራጨት ፈቃድ ሰጥቷቸው በሚዲያ በስፋት ተደራሽ በመሆን ላይ መሆናቸው ይታወቃል።     

በእስካሁኑ ሂደትም 46 የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ፍቃድ ወስደው ስርጭት የጀመሩ ሲሆን በትላንትናው ዕለትም ከ20 በላይ ተቋማት ስርጭት መጀመር የሚያስችላቸውን ፍቃድ ከባለስልጣኑ ወስደዋል።   

የሃይማኖት ሚዲያ ተቋማቱ በህግ የተጣለባቸውን ተግባርና ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም ሂደት ላይ መሆናቸው ታውቋል።    

የጄይሉ ቴሌቪዥን መስራችና የምክር ቤቱ አደራጅ አባል ጋዜጠኛ ጀማል አህመድ፤ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ፤ የምክር ቤቱ መመስረት የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ለሰላምና ለልማት የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ የሚያጎላ መሆኑን ተናግሯል።

   

የኃይማኖቶች እርስ በእርስ መተዋወቅና ተቀራርቦ መስራት ለአገርና ለህዝብ ሰላም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁሞ የምክር ቤቱ እውን መሆን የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ አደራጅ አባላት በጋራ በመሆን የማቋቋም ሂደት ላይ እየተሳተፈ መሆኑም ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቁ ላይ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጋዜጠኛ ጀማል አህመድ ተናግሯል።  

ምክር ቤቱን በፍጥነት በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሶ ከሚመለከተው አካል ፍቃድ እንደተገኘ ወደ ስራ ይገባልም ነው ያለው።

ምክር ቤቱን ከማቋቋም ጎን ለጎንም የምክር ቤት አባል የሚሆኑ የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል ብሏል።

የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን እውን መሆን አብርነትን ለማጠናከር የሚኖረው ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ ለምክር ቤቱ እውን መሆን የሁሉንም ትብብር ጠይቋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም