ቀጥታ፡

ለመከላከያ ሰራዊታችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የአሸባሪው ህወሓት ወረራን እንመክታለን-የአሶሳ ነዋሪዎች

አሶሳ ነሃሴ 26/2014/ኢዜአ/ መከላከያ ሠራዊትን በገንዘብ፣ በስንቅም ሆነ የትኛውንም አስፈላጊ ድጋፍ በማድረግ አሸባሪው ህወሃት የፈፀመውን ወረራ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዲንሳ በለው እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት ሶስተኛ ወረራውን እንደሚፈጽም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲያወጣ የነበረው መግለጫዎቹ ያሳዩ ነበር፡፡

ጦርነት የንጹሃን ህይወት እንዲሁም የሃገር ኢኮኖሚን ከማውደም ውጪ ትርፍ እንደሌለ በተግባር ታይቷል ያሉት ነዋሪው ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ሠላምን አጥብቆ ቢፈልግም ሠላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እንደማይሳካ ታይቷል ብለዋል፡፡

አሁን ያለው ብቸኛው አማራጭ ሽብርተኛውን ህወሃት አደብ በማስገዛት በሃገራችን የህግ የበላይትን ማስፈን እንደሆነ አቶ ዲንሳ አስረድተዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን ህወሃትን ብቻ ሳይሆን የትኛውንም ሃይል የመደምሰስ አቅም አለው ያሉት አስተያየት ሰጪው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረውን የአልሻባብ የሽብር ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ድባቅ መምታቱን አስታውሰዋል፡፡

"መከላከያ ሠራዊታችን ህወሃትንም እንደሚደመስስ እርግጠኛ ነኝ" ያሉት አቶ ዲንሳ ሠራዊታችን በገንዘብ፣ በስንቅም ሆነ በየትኛውም መንገድ መደገፍ እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

መንግስት በተጓዳኝ የሠላም አማራጩንም መቀጥል እንዳለበትም ነው ነዋሪው ያስረዱት፡፡

May be an image of 1 person, standing and outdoors

የህወሃት ሽብር ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ ያደረገው ወረራ የሚያሳዝን የሚያስቆጣም ነው ያሉት ደግሞ አቶ ጎሹ ጅባት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ከውስጥ ለተነሳም ሆነ ከውጪ ለመጣ ወራሪ ሃይል በታሪክ እጅ ሰጥተው አያውቁም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን ወረራ በአጭር ጊዜ ለመመከት መከላከያ ሠራዊታችን እስከ ግንባር በመዝመት ከጎኑ ቆመን መስዋእትነት የማንከፍልበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡

አቶ ክብሩ እንድሪያስ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በሀገራችን ሰርተን መቀየር የምንችለው ሠላም ሲኖር ብቻ ነው ፡፡

May be an image of 1 person, standing and outdoors

የሽብር ቡድኑ ጥፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች ጉዳት ነው ያሉት ነዋሪው ወረራውን እንደዜጋ ተቀናጅተን በመመከት ሠላማችንን መመለስ የግድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም