የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ
ነሃሴ 25/2014/ኢዜአ/ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱ በዋናነት ስራ ፈጣሪ ዜጎችን መደገፍ የሚያስችል ሲሆን፤ በሥልጠና፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንቨስትመንት ስፍራዎች ላይ ምቹ የስራ ሁኔታን መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነትን በማሻሻል ረገድ ተቋማቱ በጋራ እንዲሰሩ ያስችላል፡፡
ስምምነቱንም የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ተፈራርመዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ስምምነቱ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች የፋይናንስና ስልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
ይህም የስራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው ያብራሩት፡፡
ስምምነቱ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚወጡ ዜጎችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለውም እንዲሁ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለሥምምነቱ ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ባንኩ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ፣ ክህሎትን ማስፋት፣ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን እንዲሆን ማድረግ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በገበያ ሥርዓት ሊፈጸሙ የማይችሉ ሥራዎችን በፖሊሲ ጣልቃገብነት ተግዳሮቶችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የስራ ፈጠራ ሃሳብ ይዘው የፋይናንስ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በማገዝ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡
ዶክተር ዮሐንስ አክለውም ሥምምነቱ በሀገር ደረጃ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እንዲሁም በወጪ ንግድ ዘርፎች ላይ የተሻለ የስራ ፈጠራ እድል ለማምጣት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።