ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሓት የውሸት ወሬ ሳንሸበር ተረጋግተን የእለት ተለት ተግባራችንን እየፈጸምን ነው - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ነሐሴ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በሚረጨው ተለዋዋጭ የውሸት ወሬ ሳይሸበሩ ተረጋግተው አካባቢያቸውን በጋራ በመጠበቅ የእለት ተለት ተግባራቸውን እየከወኑ እንደሚገኙ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ኢዜአ በከተማዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት፤ መንግስት የሰጠውን የሰላም እድል አምክኖ ዳግም ጦርነት የጀመረው አሸባሪው ህወሃት ለትግራይ ክልል ህዝብ ደንታ የሌለው መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

ጸረ ሰላም የሆነው አሸባሪው ህወሓት በተለመደው የውሸት ወሬ ህብረተሰቡን ለማደናገር እየጣረ ቢሆንም እንዳልተሳካለት ገልጸው፤ የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥሬያለሁ በማለት በህዝብ ዘንድ ሽብር ለመፍጠር እየሞከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው እንዲስተጓጎል የሽብር ወሬ እየተነዛ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ ወስዶ ተረጋግቶ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሁሉም ነዋሪ በተሰማራበት መስክ ስራውን እየከወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የንግድ ስራቸውንም ያለምንም ዋጋ ጭማሬ ህብረተሰቡን እያለገሉ ሲሆን በቀጣይም ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ጨቅላ ህጻናት ጭምር ከፊት አሰልፎ የጥይት ማብረጃ ከማድረግ ባለፈ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር አገር ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት ለመመከት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ወሬ ሳንደናገር ተረጋግተን ሰላማችንና አንድነታችንን ጠብቀን ስራችንን በሰላም እየከወንን ነው ብለዋል፡፡

ሀገር በአሸባሪዎች እንዳትፈርስ ከመከላከያውና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን አስፈላጊውን ድጋፍም እናደርጋለን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ትናንት ህብረተሰቡ በሐሰት ወሬ ተረብሾ እንደነበረ አስታውሰው፤ አሁን እውነታውን ሲረዳ ተረጋግቷል ፣ ባንኮችን ጨምሮ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ክፍት ሆነው የተለመደ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ተረጋግቶ አካባቢውን በመጠበቅ የሚያከናውነውን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የውሸት ወሬ ሳይደናገርና አካባቢውን ሳይለቅ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የአሽባሪው የህውሃት ቡድን ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ኢትዮጰያን ለማፍረስ ህዝብ ለማሰቃየት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በየትኛውም መንገድ የማይሳካ ቅዥት ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለሌሎች የፀጥታ ሃይሎች አስፈላጊ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንዲያደርግ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም