ቀጥታ፡

የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በመከባበርና በትብብር በመስራት ለአገራዊ አንድነትና ለሰላም አርአያ ሊሆኑ ይገባል- የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

ነሃሴ 25/2014/ኢዜአ/ የኃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በመከባበርና በትብብር በመስራት ለአገራዊ አንድነትና ለሰላም አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  ጋር በመሆን ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ተካሂዷል።  

የውይይት መድረኩም "የኃይማኖት  መገናኛ ብዙሃን ለአብሮነት እሴቶች መጠናከር" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።    

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ የሀይማኖት መገናኛ ብዙሃን በተለይም አብሮነትን፣ ሰላምና አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የሃይማኖት  መገናኛ ብዙሃን ለትውልድ ግንባታ ለአገር ሰላም መጠናከር ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ እድሎች መሆናቸውን ጠቅሰው ተቋማቱ በመከባበርና በትብብር በመስራት ለአገራዊ አንድነትና ለሰላም አርአያ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።

May be an image of 8 people, people sitting, people standing and indoor

ከፖለቲካ፣ ከጥላቻና ከወገናዊነት ራሳቸውን ነጻ በማድረግ ለዜጎች መልካም ስነ-ምግባር መዳበር እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።   

በአንዳንድ መገናኛ ብዙሀን ዘንድ ልዩነቶችን የሚያጎሉ ስራዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመው ተገቢነት የሌለውና ለማንም የማይጠቅም መሆኑን ተናግረዋል።   

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ትኩረት መሆን ያለበት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ብቻ በመሆኑ ለባህል እና እምነት መጠናከር በመስራት መልካም ዜጋ መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።    

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የሀይማኖት መገናኛ  ብዙሃን የመከባበር መርህን ማክበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።       

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሰል ችግር በሚስተዋልባቸው መገናኛ ብዙሃን ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ ጥሪ እያቀረበ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ስማቸውን የሚመጥን ስራ እየሰሩ መሆኑን ቆም ብለው መፈተሽና ማጤን ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጸሀፊ መሱድ አደም፤ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ማድረግ ያለበቸው አገልግሎት ላይ እንጂ ፉክክር ላይ ሊሆን አይገባም ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዑዝታዝ ጀማል በሽር፤ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ከሚለያዩ ይልቅ የሚያግባቡ ስራዎችን መከወን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ፍቃድ የሚሰጠውና የሚመለከታቸው አካላት ተቋማቱ ህግን አክብረው እየሰሩ መሆኑን መከታተል አለበት ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ብርቱካን መንገሻ፤ ተቋማቱ መንፈሳዊነትን ሳያዛቡ መንፈሳዊ ህጎችን ተከትለው መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከውይይቱ በኋላም የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን መስፈርቱን ላሟሉ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የመስሪያ ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም