ቀጥታ፡

ከበቀል ጥላቻና መለያየት እሳቤ በመውጣት ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ለትውልዱ ማውረስ አለብን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ነሀሴ 25/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ከበቀል ጥላቻና መለያየት እሳቤ በመውጣት ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ለትውልዱ ማስተማርና ማውረስ አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

የትግራይ ክልል ተወላጅ ሴቶችና ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች የተሳተፉበት የአሸንዳ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የአሸንዳ በዓል ግጭቶችና አለመግባባቶች በሴቶች ፊታውራሪነት የሚፈታበትና ሰላም ወዳድነት የሚገለጽበት የሰላም መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶች አስተውሎትና ማሕበራዊ ኃላፊነት በግልጽ የሚንጸባረቅበት በመሆኑም ለሰላም ከመቼውም ግዜ በላይ አበክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ወዳድነትና ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት መሆናቸውን ጠቅሰው ይሄው ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያን የካበቱ የባህል ተውፊቶች፣ ወጎችና የአኩሪ ታሪኮች ተንከባክቦና ጠብቆ ማስቀጠል የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ብለዋለ።

የቀደሙ አያቶችን ፈለግ በመከተል አገራዊ እሴቶቻችንና ባህሎቻችንን ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ እናውል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከበቀል፣ ጥላቻና መለያየት እሳቤ በመውጣት ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትና መተሳሰብን ለትውልዱ ማስተማርና ማውረስ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በአገር ግንባታ ሂደት በጀመርነው መልኩ እጅ ለእጅ ተያይዘን በመጓዝ የተሻለች አገር ለመጪው ትውልድ ልናስረክብ ይገባል ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

የውስጥና የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያ ሰላም እንዲደፈርስና ህልውናዋ እንዲናጋ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉንም በጋራ መመከት አለብን ብለዋል።

የበአሉ ተሳታፊዎች የአሸንዳን በአል ከሁሉም አቅጣጫ ከታደሙ ወጣቶች ጋር በጋራ በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የጦርነት አማራጭ ለማንም ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ እንደሌለው የተናገሩት ወጣቶቹ ሁሉም ሰላምና አብሮነትን የመጀመሪያ አማራጭ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሸንዳ በአል በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከተማ አስተዳደሩ በማመቻቸቱም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም