ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ነሀሴ 25/2014 በአዲሱ ዓመት ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ምክክሩ ለችግሮች ተወያይቶ በጋራ መፍትሄ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት አባላቱ፣ ለቀጣይ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በየጊዜው የጥፋት አጀንዳዎችን በመፍጠር ኢትዮጵያን እያደሙ ቢሆንም የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የብልጽግናን ጉዞን እውን ለማድረግ እንደሚሰሩም አባላቱ ገልጸዋል።   

የክልሉ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ቦርጂ እንዳሉት፣ በአሸባሪው ህወሓት እንቢተኝነት ሀገራችን ተገዳ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

ህወሓት ባለፉት ጊዜያት በለኮሰው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ከመድረሱ ባለፈ ዜጎች በስጋት ውስጥ እንዲኖሩ ተጽዕኖ አሳድሮ ማለፉንም ገልጸዋል።

በህዝቦች መካከል አለመግባባት የሚፈጥሩ ችግሮችን ተወያይቶ በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደሥራ ማስገባቱን በመልካምነት አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በሥራው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ እንደ ምክር ቤት አባልነታቸው ለሀገራዊ ምከክሩ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ዳዊት ሌዳሞ በበኩላቸው፣ "ኢትዮጵያዊያን በፍቅር በጋራ ተከባብረው ያለ ስጋት በሰላም የሚኖሩባት፣ ሰርተው የሚለወጡባትና የበለጸገች ሀገር እንድትኖር ሰላም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ህዝቦች በጋራ ታግለው ያመጡትን ለውጥ ለመቀልበስ ህወሓት በቅጥረኛው ሸኔ እና ሌሎች የጥፋት ሀይሎች ታግዞ ሀገር ለመበተን አልሞ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በህዝቦች መካከል ልዩነት እንዲጎላ የሽብር ቡድኑ ያለማቋረጥ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው፣ "ኮሚሽኑ አለመግባባት የሚፈጥሩ ልዩነቶችን በማጥበብ ዜጎች ችግሮቻቸውን በንግገር እንዲፈቱ አተኩሮ ይሰራል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውንና ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አቶ ዳዊት ተናግረዋል።

ወይዘሮ መዓዛ መንግስቱ የተባሉ ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደሀገር ላለመግባባት መንስኤ ናቸው የሚባሉ ዋና ዋና ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ሀገራዊ ኮሚሽኑ ወደስራ መግባቱ ጠቃሚ በመሆኑ ኮሚሽኑ ግቡን እንዲያሳካ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።    

"ጠላቶቻችን በየጊዜው የጥፋት አጀንዳ እየፈጠሩ የህዝቦችን አንድነት ለማላላት እየጣሩ ነው" ያሉት ወይዘሮ መዓዛ፣ "ሁሌም አብሮነትን በማጠናከር ይህን ሴራቸውን ማክሸፍ ይገባል" ብለዋል።

ነባሩን የህዝብ የአብሮነት እሴት ለማስቀጠል ችግሮችን ሰከን ብሎ ማየትና ከምንጩ መፍታት እንደሚገባ የገለጹት ወይዘሮ መዓዛ፣ የጥፋት ሀይሎች ዓላማ እንዳይሳካ በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም