ቀጥታ፡

ከስምንት ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ህጻናት ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ ናቸው

አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 በኢትዮጵያ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ህጻናት ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ መሆናቸውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችና የታዩ ክፍተቶችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል። ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደገለጹት ዕድሜያቸው ከ 5 እስከ 17 ዓመት ከሆናቸው ህጻናት መካከል 8 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች የጉልበት ብዝበዛ በሚያስከትሉ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል። እርሻ፣ የቤት ውስጥ ስራ፣ አነስተኛ አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪዎችና የማምረቻ ተቋማት፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ ኮንስትራክሽን፣ የሆቴልና ቱሪዝም ስራዎች፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ማምረቻዎች ህጻናቱ በስፋት ከሚሳተፉባቸው የስራ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ። ይህ ደግሞ ህጻናቱ በስራ ላይ ለሚደርሱ አደጋዎችና ለጤና ጉዳቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ላለፉት ስምንት ዓመታት በድርጊት መርሃ ግብር የታገዘ እንቅስቃሴ ቢያደርግም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። የአገሪቱ ፖሊሲዎችና ህጎች ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ የጎላ ሚና ቢኖራቸውም በጉዳዩ ዙሪያ ተቀናጅቶ የመስራት ክፍተት መኖሩ የማስፈጸም አቅሙ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል። በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትም ሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት ህጻናትን ከጉልበት ብዝበዛ መከላከል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። የህጻናተ ጉልበት ብዝበዛን በሚመለከት ''የአገሪቱ ብሔራዊ ህጎች ምን ይላሉ?'' በሚል ርዕስ በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተዘጋጀ ጽሁፍ ለውይይት ቀርቧል። ጽሁፉን ያቀረቡት በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ አቃቤ ህግ ወይዘሪት ሊያ ተክሌ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን በሚመለከት ራሱን ችሎ በግልጽ የተቀመጠ ወንጀሉን የሚዳኝ አንቀጽ የለም ብለዋል። ህጻናት ለጉልበት ብዝበዛ ወንጀል ሲዳረጉ በሌሎች ወይም በተዘዋዋሪ ባስቀመጣቸው የወንጀለኛ መቅጫ ህጎች እንዲዳኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን ወይም የሚያሳድጉትን ልጅ ጉልበት ሲበዘብዙ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 576  ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ በኃላፊነት የሚያሳድግ ሰው በማናቸውም ምክንያት ልጁን ከአቅም በላይ ያሰራ እንደሆነ እንደሚቀጣ ይደነግጋል ሲሉ አብነት ጠቅሰዋል። አሳዳጊዎች ወይም ወላጆች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ልጆችን አሳልፈው ሲሰጡም እንዲሁ በወንጀል ህግ አንቀጽ 659 ስር በተደነገገው መሰረት ክስ እንደሚመሰረት በመጠቆም ይህም አሳዳጊ ወይም ወላጅ ግዴታውን ቸል በማለት ወይም ጥቅም በመፈለግ ለሌላ ሰው ወይም ድርጅት አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ በዚሁ አንቀጽ ክስ ይቀርብበታል ሲሉ አክለዋል። በተጨማሪም ተቋማት አልያም ድርጅቶች ለሚፈጽሙት የጉልበት ብዝበዛ በወንጀል ህግ አንቀጽ 596 ሰውን አገልጋይ በማድረግ በሚለው ስር ክስ በማቅረብ በጉልበቱ በመገልገሉ ክስ ይቀርባል ይላሉ። ከላይ በተዘረዘሩት የወንጀለኛ መቅጫ ህጎች ፍትህ ለማግኘት በተዘዋዋሪም ቢሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ዝቅተኛ በመሆኑ ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ ህጻናት የህግ ከለላ እንዲያገኙ ለማድረግ አዳጋች ሆኗል ነው ያሉት። በተለይም በተቋማት መካከል የሚስተዋለውን የተንዛዛ አሰራር በማስቀረት ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ ህጻናት የህግ ከለላ እንዲያገኙ ቅንጅታዊ አሰራርን ማዳበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ውይይቱ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በጉልበት ብዝበዛና በህጻናት ፍልሰት ላይ አስጊ ደረጃ የደረሱ ክልሎች ተሞክሮና የተገኙ ለውጦች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት መርሃ ገብሩ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም