ቀጥታ፡

ሰላምን ባለመቀበል ጦርነት የከፈተውን ቡድን የትግራይ ህዝብ በአንድነት ሊቃወመው ይገባል- የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 25/2014(ኢዜአ) የሰላም አማራጭን ባለመቀበል ዳግም ጦርነት የከፈተውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን የትግራይ ሀዝብ በአንድነት ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል ሲሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር አቶ ሱራፌል ጌታሁን ገለጹ።

ምሁሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ማወጁ የሰላም ፀር መሆኑንና ያለ ጦርነት መኖር እንደማይችል ያሳየበት ነው ።

በዚህም  የትግራይ ህዝብን ነው መከራ ውስጥ እንዲቆይ እያደረገው ነው  ብለዋል።

በተለይም የትግራይ ክልል ህፃናት፣ ወጣቶችና አቅመ ደካሞችን ለሞትና የከፋ ችግር እየዳረገ እንደሚገኝ  ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት የጀመረውን የሰላም አማራጭ በመተው አሸባሪው ህወሃት የጥፋት ድርጊቱን በግልጽና በአደባባይ ያሳየበት እንደሆነ ነው ምሁሩ የገለጹት።

ቡድኑ ጦርነትን የህልውና  ማስቀጠያ አድርጎ ስለሚወስድ ከጦርነት  ውጪ ሌላ አማራጭ አይታየውም ሲሉ  አስረድተዋል።

ቡድኑ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እያየ እንዳለየ እያለፈ ይገኛል ብለዋል።

አሸባሪው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላም ወዳድ በመምሰል የሚነዛው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ  ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳሳት በትግራይ ህዝብ ላይ መከራ እንዲበዛ እያደረገ  መሆኑን  ምሁሩ አመላክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በወቅታዊ ጉዳይ እየሰጠ ያለው ማብራሪያ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆችን ቡድኑ የሚያሰራጨውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የተለያዬ የሚዲያ አማራጭ በመጠቀም እውነቱን ማሳወቅ እንዳለባቸው ምሁሩ አንስተዋል።

የትግራይ ህዝብም ይህን በመገንዘብ የሰላም አማራጭን ባለመቀበል ዳግም ጦርነት የከፈተውን አሸባሪውን ቡድን በአንድነት ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል ብለዋል።

የፌደራል መንግስት የዜጎች ደህንነትን ለመጠበቅ የሚወሰደውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፉ ያስታወቁት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያዊያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም