ምዕመኑ በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር መሰራት አለበት-የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምዕመኑ በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር መሰራት አለበት-የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች
ሐዋሳ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሃይማኖታዊ አስተምሮ በተጨማሪ ምዕመኑ በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር በትኩረት መሰራት እንዳለበት የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች ተናገሩ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች እንደገለጹት በተለይ ወጣቱ ሀገር ለማፍረስ ታስቦ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበት ተናግረዋል።
በሃላባ ዞን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ መላከ ሃይል ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል እንዳሉት የሀገር ሰላምና አንድነት የሁሉንም የጋራ ጥረት ይጠይቃል፡፡
በመሆኑም የእምነት ተቋማት ከሃይማኖታዊ አስተምሮ በተጨማሪ ከምዕመኑም ሆነ ከመንግስት አካላት ጋር ስለ ሀገር ሰላም መምከርና በትብብር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሀገር የማስተዳደር ስልጣን የመንግስት ቢሆንም ሰላም የሁሉም ነው ያሉት መላከ ሃይል፤ ሰላም እንዲደፈርስ የሚጥሩ አካላትን መገሰጽ ከእምነት ተቋማትና አባቶች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ስለ ሀገር ሰላም ሲባል ነገሮችን በትዕግስት መመልከት ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤የኢትዮጵያዊያን እሴት የሆነውን መከባበር መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
መንግስት የሰላም አማራጭን ማስቀደሙ የሚያስመሰግነው መሆኑን አመልክተው፤ ህብረተሰቡም ይህንን በመረዳት የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይ ወጣቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎች ሀገርን ለማፍረስ የሚፈልጉ አካላት የሚያስተላልፉት መሆኑን በመረዳት ለሀገራቸው ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የስልጤ ዞን እስልምና ጉዳይ ስራ አስፈጻሚና የመስኪድ ኢማም ሃጂ ሻፊ ረዲ በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት አብሮነት በሀገር ሰላምና አንድነት ላይ ጎልቶ መውጣት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ከሃይማኖት አስተምህሮ ባለፈ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት ከምዕመኑና ከመንግስት አካላት ጋር መወያየት እና በጋራ መቆም አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የእምነት ተቋማቱም እርስ በርስ በመከባበር ስነ ምግባር ያለው ትውልድ እንዲፈጠር መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት በቋንቋ፣ በዘርና በአካባቢ የተሰሩ ስራዎች ኢትዮጵያዊያን እንዲከፋፈሉ ምክንያት መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የማእከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ኢያሱ ጣግቾ ናቸው፡፡
''እንደ ሀገር እያጋጠመ ያለው ችግር እምነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ አይደለም'' ያሉት ቄስ እያሱ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ተከታታይነት ያለው ስራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ የእምነት ተቋማት እርስ በርስም ሆነ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው በመስራት እንደ ሀገር ላጋጠመው ችግር መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የምክክር ኮሚሽንም ልዩነቶችን ለማጥበብና ወደ መግባባት ለመድረስ የሚረዳ በመሆኑ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴርና በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አማካኝነት "ሃይማኖት ለሰላም " በሚል መሪ ሀሳብ ከደቡብ፣ ሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች የሃይማኖት አባቶችና የሰላምና ጸጥታ አካላት በተገኙበት ክልል አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ተካሂዷል።