ኢትዮጵያን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሲሰሩ በነበሩ 111 ህገወጥ የዲጂታል ሚዲያዎች ላይ ክስ ተመስርቷል- የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

261

ነሐሴ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ኢትዮጵያን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሲሰሩ በነበሩና በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ህጋዊ እውቅና በሌላቸው 111 የዲጂታል ሚዲያዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የታክቲክ ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደራጁና የሽብር ወንጀሎች፣ በሙስና፣ በፋይናንስና ንግድ ነክ፣ በታክስና ጉሙሩክ ወንጀሎች ላይ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ምርመራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም መሰረት 2 ሺህ 668 ጥቆማዎችን በመቀበል 1 ሺህ 438 መዝገቦችን መርምሮ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መላካቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ሀገሪቱን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሲሰሩ በነበሩና ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ስያሜ በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ በነበሩ አካላት ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡

እነኚህ አካላት ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም በምርመራ መረጋገጡን ነው ያብራሩት።

መረጃ ተጣርቶባቸው ክስ የተመሰረተባቸው 111 የሚሆኑት የዲጂታል ሚዲያዎች በመገናኛ ብዘሃን ባለስልጣን ህጋዊ እውቅና እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የእነኚህ ህገወጥ የዲጂታል ሚዲያ ባለቤቶች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሞባይል ባንኪንግ ገንዘብ በማጭበርበር የባንኮችን መልካም ስም የማጉደፍ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ከ57 ሚሊየን ብር በላይ መዝረፋቸው በምርመራ በመረጋገጡ ክስ ተመስርቶባቸዋል ነው ያሉት።

የፌደራል ፖሊስ የአገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት በተለያዩ ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ የወንጀል ምርመራዎችን እንደሚያጣራ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም