ከምርት ጀምሮ የምግብ ደህንነትን የሚያረጋግጡ 312 አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

16

አዳማ ነሐሴ 24 ቀን 2014(ኢዜአ) ከምርት ጀምሮ የምግብ ደህንነትንና ጥራትን የሚያረጋግጡ 312 አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለፀ።

በዓለም አቀፍ የምግብ ደረጃዎች አዘጋጅ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ ዓመታዊ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ በዚህ ወቅት እንደገለፁት የስነ ምግብ ስትራቴጂና ፖሊሲውን ውጤታማ ለማድረግ ብሔራዊ የምግብ ደህንነት ደረጃዎች አዘጋጅ ኮሚቴ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባት አለበት ብለዋል ።

ከምርት ጀምሮ የምግብ ደህንነትና ጥራት ለማረጋገጥ የኮሚቴው ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእርሻ ጀምሮ እስከ ምግብ ዝግጅት ድረስ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በዚህም የምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን ሂደት ለማረጋገጥ የሚያስችል 312 አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች ተዘጋጅዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል መርዛማ የሆነው ከተፈጥሮ የሚመጣ አፍላቶክሲን ትልቅ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን ዶክተር መሰረት ገልጸዋል።

በምርት ጥራትና አያያዝ ጉድለት በበቆሎ፣ማሽላ፣ በርበሬን ጨምሮ በእንስሳት መኖ ላይ አፍላቶክሲ እየተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ጭምር አልፎ አልፎ አፍላቶክሲን ይከሰታል ያሉት ዳይሬክቴሯ ይሄ ደግሞ በዓለም ገበያ የምርት ተቀባይነትን ይቀንሳል ብለዋል ።

ይህን ችግርም ለመቅረፍ ኮሚቴው ከብሔራዊ አክሪዲቴሽን አገልግሎትና የምግብ ምርምር ላቦራቶሪዎች ፣ከዩኒቨርስቲዎች፣ አምራቾችና አቀነባባሪዎች እንዲሁም ከቁጥጥር አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል ።

በተመሳሳይ የግብርናና የታሸጉ የፋብሪካ የምግብ ምርቶች የጥራት ደረጃዎች እንዲዘጋጅና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆንም ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት ።

የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ የኮሚቴው ስራ መቀዛቀዙን የገለፁት ዳይሬክተሯ የዛሬው ምክክር የምግብ ደህንነትና ጥራትን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የደረጃዎች አዘጋጅ ኮሚቴ በአዲስ መልክ ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ መሆኑንም ገልጿል ።

የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው የተቀነባበሩና ያልተቀነባበሩ ምርቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከኮሚቴው ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የምግብ፣ መድኃኒቶችና ኮሶሞቲክሶችና ሌሎች ምርቶች ጥራትና ደህንነት ማረጋገጥ ዙሪያ ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል ።

የምግብና ስነ ምግብ ፖሊስ በመፈፀምና በማስፈፀም ረገድ በላቀ ትብብር አብረን እየሰራን ነው ያሉት ሃላፊዋ የኮሚቴው እገዛ የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደረጃዎች አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዮሴፍ ለገሰ ኮሚቴው የሀገራችን ምርቶች የተባበሩት መንግስታት የምግብ ደህንነትና የጥራት ደረጃዎች መመሪያን ተከትሎ ደረጃ እንዲዘጋጅ ያደርጋል ብለዋል ።

ምግብና የምግብ ደህንነት በተመለከተ የሚሰሩ ስራዎች በተጨባጭ በጥራት ደረጃዎች ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም