ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት ዓመት ነበር- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ነሃሴ 24/2014/ኢዜአ/ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት ዓመት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፤ በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስለነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎችና ስለተመዘገቡ ስኬቶች እንዲሁም አዲስ ዓመት ከመግባቱ በፊት በጳጉሜን ቀናት የሚከናወኑ ኩነቶች ላይ በማተኮር መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ፈተናዎች የበዙበትን ያክል በርካታ ስኬቶችና አኩሪ ድሎች የተመዘገቡበት አጋጣሚ መሆኑን አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ በርካታ ጥረቶችን ስለማድረጉ ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ሸኔና ሌሎች የሽብር ቡድኖች በምዕራብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጠላትን ተልዕኮ በመቀበል በንጹኃን ወገኖች ላይ ጥቃት ስለመፈፀማቸው አንስተዋል።

የጥፋት ኃይሎች በሰው ሕይወት ላይ ከፈጸሙት ጥቃት በተጨማሪ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማቃወስ መሰረተ- ልማትና ፋብሪካዎችን የጥቃታቸው ዒላማ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ገልጸዋል።

አሸባሪው አልሸባብ በምስራቅ ኢትዮጵያ ጦርነት በመክፈት ጥፋት ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስታውሰው፤ በቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች መመለሱን ተናግረዋል።

እንደ አጠቃላይ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን ተጋፍጣ በፅናት በማለፍ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓትና ሌሎች ጠላቶችም ያደረጉትን የጥፋት እንቅስቃሴ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ መቻሉን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት፣ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ፣ የበጋ ስንዴ ልማትና ሌሎች ሰፋፊ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት መሆኑንም አብራርተዋል።

የ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜና መሪ ሃሳብ ታስበው እንዲውሉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን አንስተዋል።

በዚህም ጳጉሜን 1 የበጎፈቃድ ቀን፣ ጳጉሜን 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአገልጋይነት ቀን እንዲሁም ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን ሆነው ታስበው ይውላሉ ነው ያሉት።

በዚህም "ጳጉሜን-01 የበጎ ፈቃድ ቀን" በሚል መሪ ሃሳብ በርካታ የበጎፈቃድ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

"ጳጉሜን-02 የአምራችነት ቀን" ሆኖ የተሰየመ ሲሆን በተለያዩ ግብርና ልማት ሥራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

"ጳጉሜን-03 የሰላም ቀን" ሲሆን በዕለቱም የኢትዮጵያዊያን የሰላም እሴቶች ይተዋወቁበታል ብለዋል።

"ጳጉሜን-04 በአገልጋይነት ቀን" ታስቦ የሚውል ሲሆን ሁሉም ተቋማት በአዲስ ዓመት በአዲስ የአገልጋይነት መንፈስ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

"ጳጉሜን-05 የአንድነት ቀን" ሆኖ የኢትዮጵያን ታላቅነትና አንድነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗን በማሳየት በልዩ ሁኔታ ይታሰባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም