ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገር አልፎ ለአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው- ዶክተር ቆስጠንጢኖስ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገር አልፎ ለአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው- ዶክተር ቆስጠንጢኖስ
ነሃሴ 24/2014/ኢዜአ/ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገር አልፎ ለአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ መሰረት እንደሚጥል የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ ተናገሩ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ህዝባቸው በጨለማ ሲኖር፣ ፋብሪካዎቻቸው በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አለመሆኑን የምጣኔ ሀብት መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም ሀገራቱ በኋላ ቀር ግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸውና ዓመታዊ ገቢያቸውም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ እሴት ያልተጨመረባቸውን ጥሬ እቃዎች በርካሽ ዋጋ በመሸጥ በፋብሪካ የተመረቱ እቃዎችን ደግሞ በውድ ዋጋ ከውጭ በማስገባት ለውጭ ምርት ጥገኛ ለመሆን ተገድደዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ከኋላ ቀር የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲላቀቁ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት አለባቸው።
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅም፤ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ የኢንዱስትሪ እድገትን ለማፋጠንና የኢኮኖሚ ሽግግርን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የህዳሴ ግድብ ቀዳሚ ግቡ የሀገር ውስጥ የ ኃይል ፍጆታን ማሟላት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይልን በሽያጭ ማቅረብ ሌላኛው ግቡ ነው።
በዚህም የቀጠናውን ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ነው የተናገሩት፡፡
በግድቡ ከቀጠናው ሀገራት ባሻገር ሌሎች የአፍሪካና የአውሮፓ አገራትንም ጭምር በኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያሉት ድጋፍ የሚደነቅ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህዝቡ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ህዝባዊ ተሳትፎውን በሌሎችም የልማት መስኮች ለመድገም ማቀድና ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቁና የሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩ በተያዘው ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ይፋ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኃይል እያቀረበች ሲሆን ለኬንያም የኃይል ሽያጭ ለመጀመር ሁለቱ ሀገራት የሽያጭ ውል ተፈራርመዋል።
በቀጣይም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ መግባባት ላይ መደረሱ ይታወቃል።