ለሀገር አንድነትና ሰላም ግንባታ መጠናከር የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር አንድነትና ሰላም ግንባታ መጠናከር የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ሐዋሳ፤ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር አንድነትና ሰላም ግንባታ መጠናከር እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ ፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱ ትውልድን በማስተማር ማህበራዊ ትስስርንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጠናከር ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስቴርም መክሯል ።
"ሃይማኖት ለሰላም " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ በሐዋሳ ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት ሃይማኖቶች የሰላም፣ የመከባበር፣ የፍትህ፣ የይቅርታና የአንድነት መሰረት ናቸው፡፡
ማህበራዊ ትስስርንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገር የመጠበቅና ትውልድን የማስተማር ሃላፊነት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
መድረኩም ሃይማኖታዊ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያለው ጠንካራ ትብብር ለሰላም ግንባታ ማዋል እንዲቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴርና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ጉዳይ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ ተመሳሳይ መድረኮች በተለያዩ ክልሎች ይካሄዳሉ ብለዋል፡፡
በችግሮች ዙሪያ ከመነጋገር ባለፈ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ለሀገር ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አወቀ አጥናፉ በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴርና የሃይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመንግስትና ለህዝብ በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ወደ ተጨባጭ ለውጥ መቀየርና ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ምክክሮችን ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የሲዳማ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ሃላፊና የሐዋሳ ከተማ ሃይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ መላከ አርያም ቀሲስ አስረስ መላኩ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት እየተሸረሸረ መምጣቱን አመልክተው፤የህዝቡን የመቻቻል እሴት ማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው መድረኩ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤በሃይማኖቶች መካከል የሚኖሩ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች በውይይትና በእውቀት የሚፈቱ በመሆናቸው በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ሃጂ መስጠፋ፤ የቤተ እምነት መሪዎች ትውልዱን ወደ ሰላም መንገድ የመምራት፣ ስለሰላም ከመስበክ ባለፈ ምሳሌ ሆኖ መገኘት አለባቸው ብለዋል፡፡
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ሃይማኖትና ሰላም በኢትዮጵያ፣ የሃይማኖትና መንግስት ግንኙነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመድረኩ ከሲዳማ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና በሰላምና ጸጥታ ላይ የሚሰሩ አካላትም ተገኝተዋል፡፡