ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና አልጀሪያ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መግባባት ላይ ደርሰዋል-አምባሳደር ነቢያት

ነሃሴ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የአልጀሪያ መሪዎች የሀገራቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር መግባባት ላይ መድረሳቸውን በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገለጹ፡፡

በአልጀሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአልጀሪያ ፕሬዝዳንት አብዱል መጅድ ታቡኔ ጋር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሁለቱ ሀገራት ከኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፈ በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ የቆየ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ፕሬዝዳንት አብዱል መጅድ፤ የሀገራቱን የሁለትዮሽና አህጉራዊ ትብብር ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ነቢያት አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጉብኝትና የመሪዎቹ ውይይት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና የህዝብን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሁሉም ወገን ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ፍላጎትና የጋራ አቋም የተንጸባረቀበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአልጀሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸው በአልጀርስ የሚገኘውን የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም በመጎብኘት በስፍራው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

በአልጀርስ የሚገኘውንና በአፍሪካ በግዙፍነቱ የሚጠቀሰውን ሳይዳል የመድሃኒት ፋብሪካንም ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም