ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው
ባህርዳር፤ ነሐሴ 23/2014(ኢዜአ) ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰሩ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡስይራ ባስኑር ገለጹ።
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ከአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አጋር ናት።
በዚህም በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ 34 የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች ውስጥ ስድስቱ በኢትዮጵያ እንደሚገኙና ይህም ከናይጀሪያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት።
ኩባንያዎቹ የተሰማሩባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎችም "ኢንዶሚንና ኑድል" በተባሉ የምግብ ዓይነቶች፣ ሳሙናና ጨርቃጨርቅ ማምረት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ባለሃብቶችም ቡና፣ ጥጥ፣ የከበረ ድንጋይና ሌሎች ምርቶችን ወደ ኢንዶኔዥያ በመላክ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮናና ሌሎች ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረውን የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነት አሁን ላይ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም በቅርቡ እንደሚካሄድ በሚጠበቅ የኢንዶኔዥያ የንግድ ዓመታዊ ኤክስፖ ላይ የኢትዮጵያ ባለሃብቶችና የንግዱ ማሀበረሰብን በስፋት ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከኤክስፖው በተጓዳኝም የሁለቱ ሀገራት ባለሃብቶች በኢኮኖሚ ጎዳዮች ላይ የሚመክሩበት ፎረም እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ በፎረሙ ከንግድ ባሻገር በኢንቨስትመንት ላይ በማተኮር የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል።
ቀደም ሲል የተካሄደው የኢንዶኔዥያ ኤክስፖ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ተነሳሽነት ተፈጥሮ እንደነበር አውስተዋል።
በቀጣይነት የሚጠበቀው ኤክስፖ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነታችን ከበፊቱ በላቀ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፉም የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመረው ግንኙነት ዛሬ ወደ 17 የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍ ብሎ በትብብር እንዲሰሩ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
እንደ አምባሳደር አልቡስይራ ገለጻ ፤ ግንኙነቱ አሁን ላይ ከ100 በላይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በተለያዩ የኢንዶኔዥያ ዩኒቨርሲቲዎች በ"ስኮላር ሺፕ " እንዲማሩም አስችሏል።
በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክም ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ያላት በመሆኑ የሚደጋገፉበትን ሃሳብ እንደሚያንጸባርቁ ገልጸዋል።
በወጣቶች፣ በንግዱ ማህበረሰብ፣ በትምህርትና በሌሎችም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እርስ በእርስ ይበልጥ በመተዋወቅ የጋራ ጥቅሞቻቸውን አጠናክረው በማስቀጠል ዘላቂ ግንኙነት ለመመስረት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን አሁናዊ ችግር በዘላቂነት በመፍታት በሰላም ተከባብሮ ለመኖር እንዲያግዝ ኢንዶኔዥያ ያላትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል።
አምባሳደሩ ሰሞኑን ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባካሄዱት ውይይት በጣናና ሌሎች የሀገሪቱ ሃይቆች ላይ የተከሰተውን እምቦጭ ለስራ እድል መፍጠሪያና ለገቢ ማስገኛ እንዲሆን እገዛ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።