የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የሚሰሩና የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ መገናኛ ብዙሃን ተጠያቂ ይሆናሉ- መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

ነሀሴ 23/2014/ኢዜአ/ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የሚሰሩና በሀሰተኛ መረጃ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ መገናኛ ብዙሃንን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ እንደሚሉት የሚዲያ ተቋማት ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም የአገረን ብሔራዊ ጥቅም የማስቀደምና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚሰሩ መሆን አለባቸው።

የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ለማህበራዊ ቀውስ የሚዳርጉና ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ግብዓት የሚውሉ መረጃዎችን ማሰራጨት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አገር በተለያዩ ምክንያቶች ፈተና ላይ ስትወድቅ የሚዲያዎች ዓላማ አገርና ህዝብን ከችግር ለማውጣት መስራት እንጂ አባባሾች መሆን እንደሌለባቸውም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የገጠማትን አሁናዊ ፈተና በድል እንድትወጣ ለሚደረገው ጥረት ሚዲያዎች አጋዥ ሆነው መቆም አለባቸው ነው ያሉት።

በሕግ ማስከበር ሂደት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ላይ ባለስልጣኑ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውሰው ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የሚሰሩና በሀሰተኛ መረጃ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ መገናኛ ብዙሃንን ተጠያቂ እናደርጋለን ብለዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ፤ ሚዲያ የአገር ጥቅም ላይ በምንም መልኩ መደራደር እንደሌለበት ይናገራሉ።

አገር አደጋ ላይ ስትሆን የሚደረግ ተግባቦትና የሚዲያ ስራም በብርቱ ጥንቃቄ መሰራት አለበት ነው የሚሉት።

በጦርነትና መሰል አስቸጋሪ ወቅቶች የሚለቀቁ መረጃዎች አገር እስከማፍረስ የሚያደርስ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን በጥንቃቄ መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

ሚዲያዎች እውነተኛና የተረጋገጠ ዘገባን ከትክክለኛ ምንጭ በማግኘት የአገር ጥቅም በማስቀደም መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም