መንግስት የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት እርምጃ ይወስዳል - ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት እርምጃ ይወስዳል - ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት
አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ዝግጅትና አቋም ላይ መሆኑን ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ። ሰሞኑን የተከሰተው ሁከት ዓላማ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ኢትዮጵያን የማያባራ የግጭት ሰለባ በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ የማሽመድመድና የመቀልበስ ሴራ አካል ነው ብሏል። ምክር ቤቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የመንግስትን ሆደ ሰፊነት እንደ አቅመ ቢስነት የተመለከቱ የጥፋት ኃይሎች የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች እየተባባሱና እየተበራከቱ መጥተዋል። በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሰሞኑን የሰው ህይወት የጠፋበትን ብጥብጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለማስቀጠል፣ በሱማሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የከሸፈባቸውን የጥፋት እቅድ በሌላ ሙከራ ለመቀጠል እንዲሁም በመስከረም መጨረሻ የሚካሄደውን የኢህአዴግ ጉባኤ ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ምክር ቤቱ አመልክቷል። ሁከቱ በትናንሽ ችግሮችና ልዩነቶች የሚነሳ ሳይሆን በታቀደ መልኩ የሚከናወን ድብቅ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው መሆኑንም ምክር ቤቱ ጠቁሟል። የሰሞኑ ሁከት ዓላማ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ወይም ግጭቶች ሲከሰቱ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማባባስና ኢትዮጵያን የማያባራ ግጭት ሰለባ በማድረግ ለውጡን ለማሽመድመድና ለመቀልበስ የሚደረግ ሴራ አካል መሆኑንም አትቷል። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከህግ የበላይነት ውጭ የሚታሰብ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያለው መግለጫው መንግስት ያለበትን የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት ለመወጣት በሙሉ ዝግጅትና አቋም ላይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል። "ስርዓት አልበኝነትን ከዚህ በኋላ የምንታገስበት ልብ፣ የምንሸከምበት ትከሻ የለንም፤ በመሆኑም ለዜጎች ህይወት ዋስትና ለመስጠት መንግስት ማንኛውንም ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን ይኸው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል" ሲል ምክር ቤቱ አስታውቋል። ወጣቱም በስሜት እየተገፋፋ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ዘራፊዎች መሳሪያ እየሆነ አፍራሽ ወደሆነ ድርጊት መምጣቱን መረዳት ይኖርበታል ሲልም አሳስቧል። አውቆም ይሁን ሳያውቅ በህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፍ ወጣትና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አውቆ ከጥፋት ተግባር እንዲታቀብ ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በመግለጫው አስገንዝቧል። የጥፋት ኃይሎች በሚያደርጉት የመጨረሻ መፍጨርጨር ለጊዜው የታወከው የህዝብ ሰላም ወደ ነበረበት እንደሚመለስም አረጋግጧል። በዚህ ሂደት ወንጀል በማቀነባበርም ሆነ ለተቀነባበሩ ወንጀሎች መሳሪያ ሆኖ የተገኘ ሰው፣ በማንኛውም ደረጃ በወንጀል ድርጊት የተሳተፈ አካል ከህግ-ሊያመልጥ አይችልም፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታም ተጠያቂ ይሆናል በማለት አስጠንቅቋል። "በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልዩነትን በሚያሰፉና ብጥብጥ በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች የምትሳተፉ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃሁን መሰብሰብ ይኖርባችኋል" ብሏል ምክር ቤቱ። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ብሄራዊራዊ የደህንነት ምክር ቤት በ08/01/2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በአገራችን እየተስተዋሉ ያሉ ህገ-ወጥና የስርዓት አልበኝነት እንቅስቃሴዎችን ገምግሞ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።
ባለፉት አምስት ወራት የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት በርካታ ስራዎች ተከናውነው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል። በዚህም መላው ህዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ተስፋ እንዲሰንቅና በሃገሩ መጻዒ እድል ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲነሳሳ አድርጓል።
ሆኖም ግን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከህግ የበላይነት ውጭ የሚታሰብ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በለውጥ ውስጥ እንደመሆናችን መጠን መንግስት ችግሮችን በሀይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ሆደ ሰፊነትን ቢያሳይም ይህን እንደ አቅመ ቢስነት የተመለከቱ የጥፋት ሀይሎች የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና እየተበራከቱ መጥተዋል።
ሰሞኑን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህን ብጥብጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለማስቀጠል፣ በሱማሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የከሸፈባቸውን የጥፋት አቅድ በሌላ ሙከራ ለመቀጠል እንዲሁም በመስከረም መጨረሻ የሚካሄደውን የኢህአዴግ ጉባኤ ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ሁከቱ ከላይ እንደሚመስለው በትናንሽ ችግሮችና ልዩነቶች የሚነሳ ሳይሆን በታቀደ መልኩ የሚከናወን፣ ድብቅ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው፣ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ወይም ግጭቶች ሲከሰቱ እነሱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማባባስ እና ሃገራችንን የማያባራ ግጭት ሰለባ በማድረግ ለውጡን ለማሽመድመድና ለመቀልበስ የሚደረግ ሴራ አካል ነው።
በመሆኑም መንግስት ያለበትን የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት ለመወጣት ማንኛውንም ህጋዊ፣ የማያዳግምና ተገቢ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ዝግጅትና አቋም ላይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ስርዓት አልበኝነትን ከዚህ በኋላ የምንታገስበት ልብ፣ የምንሸከምበት ትከሻ የለንም። በመሆኑም ለዜጎች ህይወት ዋስትና ለመስጠት መንግስት ማንኛውንም ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ወጣቱም በስሜት እየተገፋፋ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ዘራፊዎች መሳሪያ እየሆነ አፍራሽ ወደሆነ ድርጊት መምጣቱን መረዳት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም አውቆም ይሁን ሳያውቅ በህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፍ ወጣትና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አውቆ ከጥፋት ተግባሩ እንዲሰበሰብ መንግስት ያሳስባል፡፡
የጥፋት ሀይሎች በሚያደርጉት የመጨረሻ መፍጨርጨር ለጊዜው የታወከው የህዝብ ሰላም ወደ ነበረበት እንደሚመለስ መንግስት እያረጋገጠ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የደህንነት ስሜት ተሰምቶት መንቀሳቀስና መኖር እስከሚችል ድረስ፥ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን የማስከበር ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ወንጀሎቹን በማቀነባበር ደረጃም ሆነ ለተቀነባበሩ ወንጀሎች መሳሪያ ሆኖ የተገኘ ሰው፣ በማንኛውም ደረጃ ወንጀል ላይ የተሳተፈ አካል ከህግ-ሊያመልጥ አይችሉም፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በህግ ተጠያቂ ይሆናል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልዩነትን በሚያሰፉና ብጥብጥን በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃሁን መሰብሰብ ይኖርባችኋል፡፡
በመጨረሻም፥ አሁን ከጀመርነው የሰላምና የዴሞክራሲ የለውጥ መንገድ ማንም ሀይል ሊያደናቅፈን እንደማይችል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ