የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ወጥነት ላለው የመረጃ ፍሰት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - የሚዲያ ኅላፊዎች

127

ነሐሴ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት የሚዲያዎችን የመረጃ ክፍተት በመሙላት ወጥነት ላለው የመረጃ ፍሰት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ኢዜአ ያነገጋራቸው የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የስራ ኅላፊዎች ተናገሩ።

ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሸን ዘርፍ ጉባዔ የኮሙኒኬሸን አገልግሎት የ2014 በጀት የስራ አፈጻጸም ውይይት ተደርጎበታል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን እየተባለ ይጠራ የነበረው ተቋም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት በሚል በአዲስ አደረጃጀት መቋቋሙ ይታወቃል።

ከ10 ወራት በፊት ዳግም የተቋቋመው ተቋሙ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ላይ በመሆኑን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሃላፊዎች ገልጸዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው፤ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የጥላቻ ትርክቶችን ለማረም ጠንካራ ተግባቦት መፍጠር ይገባል ይላሉ።

በመሆኑም የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት በአዲስ መልክ መቋቋሙ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ገልጸው መንግስታዊ መረጃዎችን ከአንድ ማዕከል ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ፤ ተቋሙ በተለይም አገሪቷ ከነበረችብት ሁኔታ አንጻር የሚዲያዎችን የመረጃ ክፍተት በመሙላት ትልቅ ሚና ስለመጫወቱ አንስተዋል።

May be an image of 1 person, tree and outdoors

ማዕከልን መሰረት ያደረገ መረጃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በተለይም በተዛባ መረጃ እና በመረጃ እጦት የነበረውን ክፍተት በመሙላት ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ነው የተናገሩት።

ሚዲያዎች አሁንም የመረጃ ክፍተት እንዳለባቸው የገለጹት ሃላፊዎቹ በቀጣይ የመረጃ ፍሰትን በማጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ይበልጥ ተቀራርበው መስራት አለባቸው ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዕፀገነት መንግስቱ፤ የተቋሙ ዳግም መቋቋም ለህዝብና መንግስት የመረጃ ድልድይ ሆኖ እንዲሰራ አድርጎታል ብለዋል።

May be an image of 1 person

በመሆኑም የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎትና ሚዲያዎች ትብብራቸውን በማጠናከር የመረጃ ተደራሽነትን ማቀላጠፍ አለባቸው ነው ያሉት።

የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፤ ተቋሙ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን አቅም ግንባታ ዙሪያ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ በኋላ አገራዊ የኮሙኒኬሽን ስርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ የተሻለ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው በተለይም አገሪቱ ከገጠማት የመፍረስ አደጋ ለመዳን ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

May be an image of 1 person

በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መሰረት የመረጃ ቋት፣ የመረጃ ዕውቀት አያያዝና የኮሙኒኬሽን ስርዐት አለመኖር፣ በሰው ኃይል ግንባታ፣ አገራዊ የኮሙኒኬሽን ፖሊሲና ስትራቴጂ አለመኖርና የደራሽ ስራዎች መበራከት ተግዳሮቾች እንደነበሩ ተነስተዋል።

በተያዘው የ2015 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች መግባባት መፍጠር፣ በዕውቀትና በዲጂታል የታገዘ የኮሙኒኬሽን ስራ የማከናወን ግብ ተሰንቋል።

ውጤታማና ቀልጣፋ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ የተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ የተቀናጀ መንግስታዊ የመረጃ ተደራሽነት፣ ስትራቴጂካዊ የኮሙኒኬሽን ስርዓት መዘርጋት፣ የአገርና የመንግስት ገፅታ ግንባታዎች ትኩረት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

የህዝብና የተገልጋይ እርካታ ማሳደግ፣ ከአጋር አካላት ጋር መስራት፣ የፌዴራልና ክልል ተቋማት የተግባቦት የጋራ መድረኮች መፍጠር፣ አገራዊ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር ትስስርን ማጠናከር፣ ውስጣዊ አሰራርን ማጎልበትም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም