በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አርማ አጠቃቀም ላይ አዋጅ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አሶሳ፤ ነሐሴ 21 / 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አርማን ያለአግባብ በመጠቀም በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማስቀረት የአርማው አጠቃቀም አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የቀይ መስቀል ማህበርን ዓላማ የሚያስተዋውቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል  አሶሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የህግ ክፍል እና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ህግ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አስማማው ሰጠኝ በወቅቱ እንዳሉት፤  በሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ማህበሩ ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል፡፡

ማህበሩ በመላው ሃገሪቱ ያለአድልኦ የሚያቀርበው ሰብዓዊ አገልግሎት የሚያስተጓል ጉዳት መድረሱን  አውስተዋል፡፡

ጉዳቱ  በመሠረታዊነት ሊፈጸም የቻለው የማህበሩን አርማ ያለአግባብ በመጠቀም ጭምር እንደሆነ ባለሙያው ለኢትዮጵያ ዜና አግልግሎት አስረድተዋል፡፡

የማህበሩ አርማ ለህገወጥ ድርጊት አመሳስሎ በማዘጋጀት እና ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሰብዓዊ ተቋማትን አርማ በአሻጥር እና ባልተገባ መንገድ መጠቀም ወንጀል መሆኑን እንደሚደነግግ ያወሱት አቶ አስማማው፤ በተለይ የሰብዓዊ ተቋማት አርማን አስመስሎ መጠቀምን በተመለከተ ግን ህጉ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር እንደሌለ አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም የጤና ተቋማት እና የህክምና ባለሙያዎች በተለይም በግጭት  ወቅት ለሰብዓዊ ስራ ብቻ የቀይ መስቀልን አርማ በከለላነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ አርማውን ለመጠቀም ፈቃድ የሚያገኙት ግን ከማን እና እንዴት እንደሆነ በህግ በዝርዝር አለመቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

እነዚሀን የህግ ክፍተቶችን ጨምሮ የተቋሙ አርማ ያለአግባብ በመጠቀም የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር አርማ አጠቃቀም የተመለከተ አዋጅ ለማውጣት ዝግጅቱ  እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዝግጅት ስራው እየተካሄደ ያለው  ከፍትህ ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ሌሎች ተቋማት በጋራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

በመድረኩ  ከተሳተፉት መካከል መላከ ፀሐይ ቆሞስ አባዘካሪያስ ጸጋው በሰጡት አስተያየት፤ ቀይ መስቀል ከሰብዓዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስና ለህብረተሰቡ ደህንነት እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቀይ መስቀልን አርማ በማህበራዊ የትስስር ገፆች  ባልተገባ መልኩ ትርጉም በመስጠት ማህበሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲታይ የሚደረግ ጥረት መኖሩ አግባብነት እንደሌላ የገለጹት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ሼህ እንድሪ መሃመድ ናቸው።

ይህንን የሚያደርጉ   አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የማህበሩ ሰብዓዊ አገልግሎት ስራ እንዲሳካ  ከተቋሙ ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በመድረኩ  የመንግስታዊ ተቋማት አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም