አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ሰጥቻለሁ - ጂንካ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ሰጥቻለሁ - ጂንካ ዩኒቨርሲቲ
ጂንካ ነሀሴ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የአከባቢውን አርብቶ አደር ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች በ2022 በኢትዮጵያ ከሚገኙ አምስት ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
ዩኒቨርሲቲው በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት የዕጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን ከ260 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በዞኑ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
በተለይም የአካባቢውን አርብቶ አደር ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎችን ማፍለቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በእስካሁኑ ሂደት ከ170 በላይ አዳዲስ ፈጠራና ማህበረሰቡን በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎች መስራቱን ጠቅሰዋል።
ከምርምር ስራዎቹ አንዱ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ በማድረግ የአከባቢውን ማህበረሰብ ማገልገል መሆኑን ጠቅሰው "የትምህርት እድል ያላገኙ የአካባቢውን የማህበረሰብ ክፍሎችም በርቀትና በተከታታይ መርሀ ግብር ተደራሽ ለማድረግ እየተጋ ይገኛል" ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም በተለያየ የሙያ መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ260 በላይ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር ማስመረቅ መቻሉን ገልጸዋል።
የትምህርት ተደራሽነትን ከጥራት ጋር በማሳደግና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማጠናከር በ2022 በኢትዮጵያ ከሚገኙ አምስት ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን አልሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ተመራቂ ተማሪዎች በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት በአግባቡ በተግባር ላይ በማዋል ህብረተሰቡን በቅንነትእና በታታሪነት በማገልገል የሀገሪቱን የዕድገት ጉዞ ለማሳካት የበኩላቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ዶክተር ኩሴ አሳስበዋል።
የጂንካ ዩኒቨርስቲ የቦርድ አባልና የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል ።
ለሁሉም የልማትና ዕድገት ውጥኖች ስኬት ትምህርት ቀዳሚ ስፍራ እንደሚይዝ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ዞኑ ጠረፍ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑና በትኩረት ማነስ በአከባቢው የሚኖሩ ዜጎች በቂ የትምህርት ዕድል ባለማግኘታቸው የተማረው ኃይል አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል" ሲሉም ተናግረዋል ።
ይሁንና ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ አመታት የትምህርት ዕድል ያላገኙ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ክፍሎች መማርና ሙያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በአካውንቲንግ ትምህርት ክፍልና ከአጠቃላይ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁት መምህር ሚኒልክ አሰፋ ብዙ ተግዳሮት አልፈው ለዚህ በመብቃታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የጂንካ ዩኒቨርስቲ በአካባቢው መቋቋሙ ለበርካታ አመታት ሲመኙ ያላገኙትን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።
"እኔ በ53 ዓመቴ በትጋት ሰርቼ አራት ነጥብ በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ መመረቅ ከቻልኩ ወጣቱ ደግሞ እምቅ አቅምና ዕውቀት ያለው በመሆኑ ከኔ በተሻለ መልኩ በመስራት በጉልበቱና በዕውቀቱ ሀገሩን ሊያገለግል ይገባል" ብለዋል።
"ዩኒቨርሲቲው በቅርበት በተከታታይ መርሃ ግብር ትምህርት መስጠቱ ከዚህ ቀደም ትምህርት ፍለጋ ሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን ጉዞ አስቀርቷል" ያለችው ደግሞ በማኔጅመት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ምህረት ኢያሱ ናት።
ዩኒቨርሲቲው በተለይ እየሰሩ በቅርበት መማር ለሚፈልጉ ጥሩ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሳ "እኔም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆኔ ተደስቻለሁ" ብላለች ።
በተማረችበት የሙያ መስክ ማህበረሰቧን በትጋት ለማገልገል መዘጋጀቷን ትናግራለች።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል ።
በስነ ስርአቱ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
ከ4ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት በ29 የትምህርት ክፍሎች ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና ተከታታይ መርሃ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ አመላክቷል።