ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን በትምህርት ያገኙትን እውቀት የሀገርን ችግር መፍቻነት ማዋል ይገባቸዋል--ዶክተር ፍሬው ተገኘ

ባህር ዳር ነሃሴ 21/2014 (ኢዜአ) የዩኒቨርሲቲው የዛሬ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት የሀገርን ሁለንተናዊ ችግሮች መፍቻነት ማዋል እንደሚጠበቅባቸው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ አስገነዘቡ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ እንደገለጹት በምረቃ ሰነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ተመራቂዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ለምርቃት መብቃታቸው የጥንካሬያቸው ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ያልተነካ እምቅ ሃብት ያላት ሀገር ናት ያሉት ዶክተር ፍሬው ሀብቱን አልምቶ የሀገርንና  ህዝብን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በሳይንስና ቴክኖሎጅ የበለጸገ ትውልድ ማፍራት ይገባል ብለዋል።

በሀገራቸን እያጋጠሙ የሚገኙ ሰውሰራሽና የተፈጥሩ መሰናክሎች በራሳችን አቅም ልንፈታ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም ዩንቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃችሁ ተማሪዎች በቆይታችሁ ያገኙትን እውቀት ለችግሩ መፍቻነት ለማዋል መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው  ለሰሜን ወሎ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳድር ዞኖች ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጽእ አቡነ ኤርሚያስና ለኢትዮጵያ አትሌትክስ ፈዴዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት  ኮማንደር  ደራርቱ ቱሉ  የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸውም አቡነ ኤርምያስ በሃይማኖት አባትነታቸው የተማሩትንና  ያስተማሩትን  ሰውን በሰውነቱ ብቻ በማክበር በተግባር በማስመስከራቸው መሆኑን አስረድተዋል

አትሌት ኮማንደር ደራርቱም በአትሌትነት ዘመኗ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተደጋጋሚ ድል በማስመዝገቧና አሁን ላይም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዘርፍ በመምራት ለድል በመብቃቷ መሆኑ ተመላክቷል።

"ዩንቨርሲቲው ያበረከተላት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ ሁሉ አትሌቶች ጭምር ነው" ያለችው ደግሞ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ናት።

"የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት በቀጣይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የበለጠ ስራ እንድሰራና ውጤት እንዳስመዘግብ ተነሳሽነትን የሚፈጥርልኝ ነው" ብላለች።

የሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ ተመራቂው ናትናኤል ማህረ በበኩሉ ኢትዮጵያን ከችግር በማውጣት ለማሳደግ ከኛብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

በዩንቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን የኮምፒተር ሳይንስ እውቀት ለሀገር እድገት ለማዋል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመረቁበት የትምህርት መስክ ከመሰል ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር ከወዲሁ ማቀዳቸውን የገለጸችው ደግሞ የጋርመንት ምህንድስና ተመራቂዋ ተማሪ ሳባ ተስፋው ናት።

ለራሳቸው የስራ እድል ለመፍጠር ከማሰብ ባለፈ የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አመራር አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራንና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 1 ሸህ 902 ተመራቂዎች ሴቶች ሲሆኑ ከነሱም መካከል አራቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም