መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ
ጎባ ፤ ነሐሴ 21/2014(ኢዜአ)፡- መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በብዝሃ ህይወትና ጤና ሳይንስ መስኮች የልህቀት ማዕከል ለመሆን የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሙያ ያሰለጠናቸው 356 ተማሪዎችን ዛሬ ሲያስመረቅ፤ ከመካከላቸውም 15ቱ በህክምና ዶክትሬት ደረጃ የተማሩ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመደበኛነት ከሚያካሄደው የመማር ማስተማር በተጓዳኝ በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አበረታች ተግባራትን እያከናወና ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ምርምር ላይ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በብዝሃ ህይወትና የጤና መስኮች የልህቀት ማዕከል ለመሆን የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ዶክተር አህመድ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ተመራቂዎች ኅብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነት ተጥሎባችኋል” ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም በበኩላቸው፤ በተለይ ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች ዘርፉ የሚጠይቀውን ሥነ- ምግባር በመላበስ ኅብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ከራስ ጥቅም ይልቅ ለወገን ቅድሚያ መስጠት፣ ብልሹ አሠራሮችን መከላከልና ውጤታማ ሥራን በማከናወን ለሌሎች አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ዶክተር ጄይላን እንዳሉት፤ ሆስፒታሉ በህክምና ሳይንስ ዘርፍ እያከናወነ ካለው የመማር፣ ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በተጓዳኝ ለህሙማን በሚሰጠው የጤና አገልግሎት ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
ሆስፒታሉ ያለበትን የቦታ ጥበት ችግር ለማቃለል እያስገነባ ያለው ባለስምንት ወለል ህንፃ አሁን ላይ አፈጻጸሙ ከ92 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
ሆስፒታሉን በዘመናዊ ዕቃዎች ለማደራጀት በመንግስት በጀት ብቻ አስቸጋሪ በመሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶክተር ጄይላን ጠይቀዋል፡፡
ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል በከፍተኛ ማዕረግ በዶክትሬት ደረጃ የተመረቀው ያህያ አብደላ በሰጠው አስተያየት "የጤና ሥነ- ምግባርን በማክበር ኅብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል።
በተለይ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የተያዘውን የጤና ልማት ግብ ለማሳካት የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጿል።
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ሳይጨምር ባለፉት ዓመታት ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁን ተቋሙን በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡