ለሰላም ማንኛውንም ዋጋ ልንከፍል ይገባል-- አቶ ብናልፍ አንዷለም የሰላም ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ማንኛውንም ዋጋ ልንከፍል ይገባል-- አቶ ብናልፍ አንዷለም የሰላም ሚኒስትር
ባህርዳር ነሐሴ 21/2014 (ኢዜአ) ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትገሰግሳለች፣ ሰላምና ደህንነት ስለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ 10ኛውን የፎቶ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም "የሰላም ግንባታ ስኬቶችና ፈተናዎች" በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመወያያ ፅሁፍ ለሰው ልጆች ዋነኛው የመኖር ዋስትና ሰላም መሆኑን አመልክተዋል።
ሰላም ከሌለ ህዝቡ ወጥቶ ስራውን በአግባቡ ሰርቶ ለመመለስ ፈተና እንደሚሆንበትና የሀገሪቱን ዕድገትና ብልፅግና ማረጋገጥም እንደማይቻል ጠቅሰዋል።
"የኢትዮጵያ መልማትና ማደግ የማያስደስታቸው የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ሆነው ሰላሟ እንዳይረጋገጥና ልማቷ እንዳይፋጠን ተቀናጅተው እየሰሩ" ሲሉም አመልክተዋል።
"ተገደን ካልሆነ ጦርነት አውዳሚ ነው" ያሉት አቶ ብናልፍ "የሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥም ለሰላም አስፈላጊውን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ልንሆን ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
አሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልል በፈፀመው ወረራ በርካታ ዜጎች መገደላቸውንና በርካታ ዜጎችም መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።
"መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ችግሮችን እንፍታ ቢልም አሁንም አሸባሪው ህወሃት አሻፈረኝ በማለት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቷል" ብለዋል።
"ሀገራችን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ተላቃ ሰላምና ደህንነቷ በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ሁላችንም ለሰላም የሚከፈለውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።
"አሸባሪው ህወሃት የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋገጥ ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር ዳግም ጦርነት ከፍቷል"ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።
"የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና የገጠመንን ፈተና በድል ለማጠናቀቅ መንግስት መላ ህዝቡን በማሳተፍ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ ይገኛል"።
"ጥቅምና ፍላጎቱን በህዝቦች ላይ በኃይል ለመጫን የተዘጋጀ ኃይል እስካለ ድረስ ጦርነት አይቀርም" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ መንግስት አሸባሪውን ቡድን በመመከት የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉአላዊነትና ሰላም የማስጠበቅ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሀገራችንን ለማፍረስ ተቀናጅተው የሚሰሩ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ መክተን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል "ብለዋል።
"ድርጅቱ ስለኢትዮጵያ ያዘጋጀው የዛሬው 10ኛ መድረኩ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈዓሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።
እስካሁን በተዘጋጁ መድረኮችም ሰላምና ደህንነት ስለኢትዮጵያ በሚሉና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ ስለአካባቢው ሰላምና ደህንነት እንዲያስብ፣ የሀገሪቱ ልማትና ዕድገት እንዲፋጠን የሚደረጉ የውይይት መድረኮች የሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም በቀሪ ሁለት ከተሞች ስለኢትዮጵያ የፎቶ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይቶች እንደሚካሂድ አቶ ጌትነት አስታውቀዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህሯ ዶክተር ፍቅርተ አዱኛ በበኩላቸው "የሰላም ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል።
"የትምህርቱ መሰጠት የግጭት አፈታት ክህሎትን ልጆች ከታች ጀምረው በማዳበር እንዲያድጉ ያስችላል" ሲሉም አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለና የሰላም ሚኒስትሩ ቶ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።