የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ምዕዋለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎታቸው ጨምሯል

89
አዲስአበባ 8/2011 በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ማሻሻያዎች የፈረንሳይ ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፍላጎት መፍጠራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬደሪክ ቦንተምስን ትናንት በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ፕሮፌሰር አፈወርቅ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህል፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗም አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬደሪክ ቦንተምስን በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ መጎልበት እንደሚገባው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉት ማሻሻያዎች የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ  ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳደሩባቸውም ነው ያስታወቁት። ማሻሻያዎቹ ከኢትዮጵያ አልፈው በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እያመጡ መሆኑንና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድም አዎንታዊ ትኩረት እንደሳቡ አምባሳደሩ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም