ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ10ኛ ዙር "ይቆጥቡ ይሸለሙ" መርሃ ግብር ባለእድለኞች እጣ ይፋ ሆነ

ነሀሴ 21/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ10ኛ ዙር "ይቆጥቡ ይሸለሙ" መርሃ ግብር ባለእድለኞች እጣ ይፋ ሆነ ።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች፣የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳዳሪና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ወቅት ባንኩ ላለፉት 80 ዓመታት የዜጎችን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ የበኩሉን ሚና ሲወጣ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ-ግብር አማካኝነት የቁጠባ ባህል እንዲዳብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ10ኛው ዙር ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር እና የ21ኛ፣22ኛ እና 23ኛ ዙሮች የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ  141 ሽልማቶች ለባለ እድለኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም፣ 2 ባለ ሶስት መኝታ የመኖሪያ አፓርትመንቶች፣ 13 አውቶሞቢሎች፣ 36 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችና 90 ላብቶፕ ኮምፒዩተሮች ለባእድለኞች ተበርክተዋል ነው ያሉት።

የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ902 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቷ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከግማሽ በላይ የገበያ ድርሻ እንዲኖረው አስችሎታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 1ነጥብ 2 ትርሊዮን ብር መድረሱን አብራርተዋል።

ባንኩ ትላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ የመደገፍና ለህብረተሰቡ የቀን ተቀን ኑሮ መሰረታዊ የሆኑ ማዳበሪያና የነዳጅን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦችን ከውጭ እንዲገቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ ይህን ሀላፊነቱን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ደንበኞች በሀገራዊ የልማት ስራ ውስጥ የራሳቸውን ትልቅ ሚና እየተወጡ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቷ የልማት መስክ  ትልቅ ሚና እየተወጣ ያለ ባንክ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ባንኩ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን በሁሉም የባንክ መመዘኛ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ 

በእለቱ ሽልማቱን ያገኙ ቆጣቢ ባለ እድለኞች በባንኩ በመቆጠብ ከማትረፍ ባሻገር ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የባንኩን አገልግሎት መስፋፋት ተከትሎም 36 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች የቁጠባ ሂሳብ መክፈታቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም