ቀጥታ፡

''አሸባሪው ሕወሐት የሰላም አማራጮችን ሁሉ ረግጦ የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አባብሶ ቀጥሎበታል” ፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አሸባሪው ሕወሐት የተዘረጋለትን የሰላም አማራጭ ረግጦ ለሦስተኛ ጊዜ በሀገራችን ላይ የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
አሸባሪው ለሰላም የተዘረጋውን መንገድ ትቶ፣ በሙሉ ዐቅሙ ለጦርነት ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወቃል።አሁንም በተለያዩ ግንባሮች የከፈተውን ጥቃት አድማሱን በማስፋፋት ለፍቶ አዳሪ ንጹሐን ዜጎችን ዒላማ እያደረገ ይገኛል፡፡
ጊዜ ያለፈበትን የሰው ማዕበል የጦርነት ስልት በመከተል በሺዎች የሚቆጠሩ አዳጊዎችንና ወጣቶችን በገፍ እየማገደ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ዛሬም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ሕወሐት ግድያ፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ማውደም፣ መሠረተ ልማት የማፈራረስና መሰል የጭካኔ ተግባራትን ለመፈጸም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ኃይል አሰባስቦ ወደ አማራና አፋር ክልል አዋሳኞች እየተንቀሳቀሰ ነው።
መንግሥት የዘረጋው የሰላም አማራጭ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይህ አሸባሪ ቡድን የከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት በተሟላ ብቃት በመመከት ላይ ይገኛል።
ነሃሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም