ህብረቱ በአንዳንድ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረቱ በአንዳንድ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘ
አዲስ አበባ መስከረም 8/2011 በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ፣ ከታ፣ አሸዋሜዳ፣ አንፎና አካባቢ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታወቀ። ህብረቱ ዘር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከትን መነሻ በማድረግ በዜጎች ላይ በተፈጸመውን ግድያ፣ ጥቃትና ዘረፋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ይህ አይነቱ እኩይ ተግባር ለረጅም ጊዜ ተከባብሮና ተዋዶ የኖረውን ህዝብ ለማጋጨት የሚደረግ በመሆኑ በጽኑ ሊወገዝ እንደሚገባ ህብረቱ አሳስቧል። ዜጎች ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲኖሩ መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙትን በመከታተል ለህግ ማቅረብና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዳለበትም ህብረቱ አስታውቋል። የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም እንዲህ ያሉ ተግባራትን ምዕመኑ እንዲያወግዝና ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማስተማር አለባቸው ብሏል። ህብረቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም በመግለጫው አመልክቷል።