መንግሥት በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያመላክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያመላክት ነው
ነሐሴ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)መንግሥት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያመላክት መሆኑን የቀድሞ ሠራዊት አባል የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ፡፡
ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ወደጎን በመተው ጦርነት መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን እያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎችና ሲያሰራጫቸው የነበሩ የሐሰት መረጃዎች ቡድኑ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር በግልጽ የሚያሳዩ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በዛሬው እለትም ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ተመቱብኝ ብሎ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ትናንት ሲታወቅበት የነበረውን ባህሪ በማስቀጠል ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ይህን የውሸት ፕሮፓጋንዳውንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረዳው ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
"የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጥንት ጀምሮ በወታደራዊ ዲሲፕሊን ይታወቃል" ያሉት ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ፤ ከዚህ አኳያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ አሁንም እንደለመደው የሐሰት መረጃ እያሰራጨ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም የሽብር ቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ቡድኑ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ ድጋፍ ይውል የነበረን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ ደግሞ ለሕዝብ ደንታ የሌለው መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ቡድኑን ከማውገዝ ጎን ለጎን የዘረፈውን ነዳጅ እንዲመልስ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡