አሸባሪው ህወሓት ዳግም ጦርነት በመቀስቀስ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ዳግም ጦርነት በመቀስቀስ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ ይገባል
ነሃሴ 20/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሓት ዳግም ጦርነት በመቀስቀስ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደራጀ መልኩ ማሳወቅ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የአመራር አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረቱ ያደረገ ሥልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናውን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ባለሥልጣን በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፤ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አማካሪ ተስፋዬ ሽፈራው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለአገር ሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ከሰሞኑ አሸባሪው የህወሓት ቡድን መንግሥት ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት በመክፈት ለኢትዮጵያ ሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የሽብር ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን ዳግም ለስደትና መፈናቀል እንዲዳረጉ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉሱ ለገሰ፤ ሥልጠናው ወደ አመራር እየመጡ ለሚገኙና በአመራርነት ላይ ያሉ አካላት ያላቸውን እውቀት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
በተለይም የወጣቶች የአመራርነት ብቃት ከፍ እንዲልና ሕዝቡንም ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እንደሚያግዛቸውም ጠቁመዋል፡፡
አካዳሚው ከመንግሥት ሠራተኛው ውጭ የግሉንና ሲቪል ማኅበረሰቡን በእኩል እንዲያገለግል ተልዕኮ መውሰዱን የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ናቸው፡፡
በዚህም አካዳሚው በአመራርነት ላይ ያሉ አካላትን አቅም ማዳበርና ወደ አመራርነት የሚመጡትን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቷ የሚታየው የለውጥ ሂደት ዘላቂ ሆኖ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ የሲቪል ማኅበረሰቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡