ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን በኃይል ወስዶ ለጦርነት ሲያውል እንደነበር ተገለጸ

ነሐሴ 20 ቀን 2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሆኑ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን በኃይል ወስዶ ለጦርነት ሲያውል እንደነበር ተገለጸ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ምንም አስቻይ ሁኔታዎች አልፈጠረም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡


በዚህም አገሪቱን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ከማሳጣቱም ባለፈ የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ክልል ሕዝቦች በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት እንዲሰቃዩ አድርጓል፡፡


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ መሬት ላይ የወረደ ተግባር አልፈጸመም።


ቀደም ሲል አሸባሪው ቡድን በትግራይ ክልል ለጥገና የገቡ ስድስት የኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞችን አፍኖ ወስዶ እስካሁን የገቡበት እንደማይታወቅ ነው የገለጹት።


እንዲሁም ለጥገና ሥራ የሚውሉ የኤሌክትሪክ ኃይሉን ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን በኃይል ወስዶ ለጦርነት ተጠቅሞበታል ብለዋል።


ከአፈና እና ከጥይት እሩምታ ሸሽተው ወደ አገር ቤት የመጡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች ለከፍተኛ የስነ-ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።


ከቀደመ ግብሩ ሳይታረም ዳግም ጦርነት የቀሰቀሰ ቡድን የኤሌክትሪክ ሠራተኞቹ ወደ ክልሉ ገብተው ጥገና እንዲያደርጉ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሬያለሁ ማለቱ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስረድተዋል።


አሸባሪው ቡድን በቅርቡ ለረድኤት ሥራ የገቡ ነዳጅና የነዳጅ ቦቴዎች እንዲሁም ለሕዝቡ በሚላኩ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ እያደረገ ያለውን ዘረፋ በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ውግዘት እየቀረበበት እንደሆነ ይታወቃል።


ይህንና መሰል ተግባራት እየፈጸመ ያለው ቡድን የትግራይ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ለመንግሥት ዋስትና ሰጥቻለሁ ማለት ከእውነት የራቀ ነው።


አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል የማግኘት መብቱን ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመበት መሆኑን የትግራይ ሕዝብ ሊገነዘብ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።


ተቋሙ የዜጎች ኤሌክትሪክ የማግኘት መብት ለድርድር መቅረብ አለበት ብሎ እንደማያምንና፤ አስቻይ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ አገልግሎቱ በማንኛውም ሰዓት ለጥገናው ሙሉ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው አክለዋል።


በጦርነቱ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው በአፋርና በአማራ ክልል ያሉ አንዳንድ ዜጎች እስካሁን ኤሌክትሪክ እያገኙ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።


የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመረትባቸው ቦታዎች በባህሪያቸው ዝቅተኛና ፈታኝ የሆኑ፣ ረዣዥም ከፍተኛ ቦታዎችን መውጣት የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል።


ለሕዝብ ጥቅም የቆምኩ ነኝ የሚል ማንኛውም አካል መሰረተ-ልማት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሊከላከልና ከውድመት ሊታደገው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም