ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሕግ ማሻሻያዎችና ዲጂታል አሰራሮች እየተተገበሩ ነው

ነሐሴ 20 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሕግ ማሻሻያዎችና ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድና ድኅረ- ፈቃድ ምርመራ ረቂቅ መመሪያ በተመለከተ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ምክክር አካሂዷል።

በምክክሩም ረቂቅ መመሪያው የኢትዮጵያን ንግድና ኢንቨስትመንት ውጤታማ በማድረግ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ተገልጿል።

በምክክሩ ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ሐሰን ሙሀመድ፤ ኢትዮጵያን በንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ አገር ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በንግድና ኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥና ውጭ ባለሃብቶች የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በኦንላይን ባሉበት ቦታ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፌደራል እስከ ወረዳ ለሚገኙ 1ሺህ 463 የንግድ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት በንግድና ኢንቨስትመንት የተሰማራ ማንኛውም አካል ባለበት ቦታ ሆኖ በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት የሚያገኝበት አገር አቀፍ ሥርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።

ንግድና ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድገት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የዘርፉን አገልግሎት ማሳለጥ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ መደረጉንም እንዲሁ።

ለአብነትም በዚህም 60 ዓመታት ያስቆጠረውን የንግድ ሕግ በአዲስ መልክ ማሻሻያ በማድረግ አሳሪ የነበሩ አንቀጾችን መሻሻል እንደተደረገባቸው ጠቁመዋል።

የንግዱን ሥርዓት በማሳለጥ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር እንዲታገዝ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የነዳጅ ድጎማ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦችና ሌሎች ግብይት ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ማጽዳት የሚያስችል የኦንላይን ሥርዓት እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ የውጭ ባለሃብቶች መሳብ የሚችል ቀልጣፋና ምቹ የንግድ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር መወዳደር የሚችሉበትን መመሪያ በማዘጋጀት ፈጣን የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን ለማሻሻል እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች መልካም ቢሆኑን አፈጻጸማቸው ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ እና ድኅረ-ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ ላይ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ምክክር ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም