የአፍሪካ እና የቻይና መገናኛ ብዙሃን ትብብራቸውን በማጠናከር የአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት እንዲጎለብት ሊሰሩ ይገባል-አምባሳደር ተሾመ ቶጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ እና የቻይና መገናኛ ብዙሃን ትብብራቸውን በማጠናከር የአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት እንዲጎለብት ሊሰሩ ይገባል-አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
ነሃሴ 20/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ እና የቻይና መገናኛ ብዙሃን ትብብራቸውን በማጠናከር የአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት እንዲጎለብት ሊሰሩ እንደሚገባ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።
አምስተኛው የቻይናና የአፍሪካ የመገናኛ ብዙኃን ትብብር ፎረም የቻይና የመስኩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮችና ከቻይናና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞች በተገኙበት ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ የአፍሪካና የቻይና ትብብርንና ግንኙነትን በተመለከተ የሚራገቡትን የተሳሳቱ መረጃዎች ለመመከት በጋራ መሥራት ይገባል።
የቻይናና የአፍሪካ የመገናኛ ብዙሃን የየራሳቸውን አገራት የተመለከቱ መረጃዎችን በራሳቸው እይታና እውነታውን በሚያሰርጽ መንገድ አሳሳች መረጃዎችን በሚከላከልና በሚመክት አግባብ መዘገብ ይገባቸዋል ብለዋል።
ይህም በተለይም የአፍሪካና ቻይና ትብብርን በተመለከተ የሚናፈሰውን የተሳሳተ መረጃ ለመቀልበስ እንደሚረዳ አስገንዝበው ለዚህም በአፍሪካ በቻይና በመስኩ ያለው ትበብር መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
በአፍሪካና በቻይና በመገናኛ ብዙሃን በተለይም በዜና ሽፋን፣ በአመራር፣ በስርጭት ጣቢያ ልማት፣ በይዘት ሥራ፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በሥልጠና የጋራ መርሃ ግብሮች በመቅረጽ ተብብሩ ሊጠናከር እንደሚገባው ነው አጽንጾት የሰጡት።
ይህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ከተመሰረተው የአፍሪካና የቻይና የትብብር ማዕቀፍን ባገናዘበ መልኩ በጋራ ተጠቀሚነትና እኩልነት መርህ መፈጸም እንዳለበት በመጠቆም።
የአፍሪካና የቻይና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ትብብር የጋራ ልማትና ብልጽግና ለማምጣት እንዲሁም በሁለቱ ወገን መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብታዊ፣ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ሌሎች የትብብር መስኮችን የተመለከቱ አውነታዎችን ለዓለም ለማሳየት ይጠቅማል ብለዋል።
የቻይናና የአፍሪካ የመገናኛ ብዙሃን ትብብር በአፍሪካ ቻይና የትብብር ማዕቀፍ ትልቅ ሥፍራ መያዙን የጠቀሱት አምባሳደር ተሾመ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ በበኩላቸው፤ የቻይናና የአፍሪካ የመገናኛ ብዙሃን በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በተለይም ደግሞ በሁለቱ ወገን ኅዝቦች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር፤ የእኩልነትና ፍትህ ጠበቃ በመሆን ለዓለም ልማት ሊተጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቻይና እና አፍሪካ ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ጠቁመው በሁለቱ ወገን ያሉት የመገናኛ ብዙሃን የጋራ ሥምምነትና ትብብር እንዲኖር መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በተለይም የዓለምን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንዲሁም የጋራ ራዕይ ያላቸው ማኅበረሰቦች ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ በጋራ ሊሰሩ የሚገባቸው መስኮች መሆኑን አንስተዋል።
የቻይና አፍሪካ የሚዲያ ፎረም ከተመሰረተ ዘንድሮ አስር ዓመት ሆኖታል፤ እስካሁን 3 ሺህ የሚጠጉ የአፍሪካ ጋዜጠኞች በቻይና የሙያ ሥልጠና መውሰዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።